Thursday, February 13, 2014

ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?

በተለያዩ ዘመናት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ይቅርታ፣ ቸርነትና ምህረት በቅዱሳኑ በኩል ገልጿል። ከዚህም አንዱ ለሰብአ ነነዌ ያደረገላቸው ምህረትና ይቅርታ ሲነገር ይኖራል። በትንቢተ ዮናስ ተጽፎ እንደምናገኘው የነዚህ ህዝቦች ኃጢዓትና በደል በእግዚአብሔር ፊት ደርሶ ነበር ,,  የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ።ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ ,, ት ዮና 1፥1 ,, በዚህም የተነሳ ነቢዩ ዮናስን ወደ እነርሱ ልኮት ነበር። ነገር ግን ነቢዩ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከመፈጸም ይልቅ በራሱ ሃሳብ ተሸንፎ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ሞከረ። ብዙውን ጊዜ በራሳችን እውቀትና ጥበብ ከእግዚአብሔር ለመሸሽ የምናደርገው ሙከራ ሰው ምን ያህል በራሱ ሞኝ እንደሆነ የሚገለጥበት ነው። የሚገርመው በእውቀትና በጥበብ የተሻሉ ሆነው በሰው ዘንድ የሚታዩ በእግዚአብሔር ተመርጠው ለህዝቡ እረኛ የሆኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ሲሞክሩ እጅግ ይደንቃል። ዮናስም እንዲሁ ነበር ያደረገው። እግዚአብሔር ደግሞ ከተናገረ ያደርገዋል፣ ከጀመረም ይፈጽማል። ዮናስ በራሱ ጥበብ ከእሱ ለማምለጥ ቢሞክርም በጥበበ እግዚአብሔር ከጥልቁ ባህር እና ከአሳ አንበሪ ሆድ በሰላም እንዲወጣ አድርጎት ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን የንስሃ ጥሪ አድርሶላቸዋል።


የነነዌ ሰዎች የሰሩት ኃጢዓት በዝርዝር ባይጻፍም ክፉ ስራ እንደሰሩ ተገልጿል።  እግዚአብሔርም አስቀድሞ የንስሃ ልቦና እንዳላቸው በማወቁ መጥፋታቸውን አልፈለገም። ነቢዩ እንደታዘዘው ንስሃ እንዲገቡ ነግሮ ሄደ። ጥሪው የእግዚአብሔር መሆኑን አምነው ጥፋታቸውን ተረድተው ከንጉሱ እስከ ጡት የሚጠቡ ህጻናት ድረስ። ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው በጾም በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው ንስሃ ገቡ። እንስሳት ስንኳ ከምግብ እንዲከለከሉ ንጉሱ አዋጅ እንደነገረ ተጽፏል  እግዚአብሔርም ከቁጣው አዳናቸው። ዛሬ ላይ መናፍቃን እንኳን ለእንስሳው ለክቡሩ የሰው ልጅ የጾም አዋጅ በመታወጁ ሲተቹ ይሰማሉ ባለመረዳታቸው ነው  ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ እንደተናገረው ,, ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር 1ኛ ቆሮ 2፥8

በዘመናችን አዋጅ የሚነግር ነቢይ ወይም ወንጌል የሚስብክ ሐዋርያ አይደለም የጠፋው። እግዚአብሔር ትክልል ነው ፣ ህጉ ተጥሷል ብሎ በንስሃ የሚመለስ ልቦና ስለሌለ ነው ። ዛሬ ላይ ያለን መልእክተኞች እንደ ዮናስ ከባህር ገብተን የምንወጣ ሳንሆን በዚያው ሰምጠን የምንቀር ነን። በጥፋት ውሃ ዘመን ኖህ እንደላከው ቁራ ምግብ ፍለጋ ስንዋትት ዘመኑ የሚያልፍብን  የቁራ መልእክተኞች ነን። ታዲያ እግዚአብሔር ማን መልዕክቱን ያድርስለት? እግዚአብሔር ከባህር አውጥቶ ነቢይ እንዳይልክልን የኛ ልቦና በጥላቻና በተንኮል የተሞላ እንደሆነ እሱ ያውቀዋል።
 
መቸም ሰው ለመጸጸትም ሆነ እግዚአብሔርን ይቅርታ ለመጠየቅ መጀመሪያ በደለኛ መሆኑን ማመን አለበት። እኛን ከነነዌ ሰዎች የሚለየን የምንፈጽመው ክፉ ስራ ለኛ አለመታየቱ ነው። ለንስሃ የሚጠራ ሐዋርያም ቢነሳ እንኳን ሁሉም እኔን አይመለከትም ነው የምንለው። ከላይ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተቀመጡት ጳጳሳት እንኳን ሳይቀር እርቅን እምቢ ብለው እየኖሩ ያሉት የሚነግራቸው አጥተው ሳይሆን እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ነው። ምናልባት በዘመናችን ክፉ ስራ እየተሰራ ነው ብለው ያምናሉ ብንልም  የሌሎችን ኃጢአትና በደል ከመናገር ያለፈ አይደለም። 
 
ስለ ነነዌ ሰዎች የንስሃና የጾም አዋጅ በትንቢተ ዮናስ ከምዕራፍ 1 ጀምሮ በሰፊው ተጽፏል። እግዚአብሔር እንዴት ከጥፋት እንደታደጋቸው ተረድተን እኛም ከጥፋት የምንድንበትን መንገድ እንያዝ።  
 
በየዘመኑ እንደሚነሱትቅዱሳን ሰዎች ዛሬም ላይ ከሁሉም ክፍል በጎና ፈራሄ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሰዎች አሉ።  እርቅና  ሰላምን ለማምጣት የሚጥሩ ነገር ግን ጥቂቶች ስለሆኑ ይሸነፋሉ። ከላይ እስከታች ድረስ እርቅና ሰላምን ባህላችን እስካላደረግን ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር እየኖርን ነው ልንል አንችልም። መለያየትን እንደመፍትሄ የምንጠቀም ከሆነ ትልቁን የፍቅር ህግ እንደሻርን መገንዘብ አለብን። ህዝብና አህዛብን በፍቅሩ አንድ ያደረገውን ጌታም መርሳት ነው።
 
በሃገራችን ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ ነገር አለ ,, ይቅር ለእግዚአብሔር ,,   መባባል ትልቁ ሃብታችን ነበር። ዛሬ ላይ እንደጎጅ ባህል ተቆጥሮ አትድረስብኝ አልደርስብህም  በሚለው ዘመን አመጣሽ የምእራባውያን ባህል እየተያዝን ነው። መተማመን በጎደለው ጉርብትና ከመኖር ይልቅ እንደቀድሞው በአንድ ገበታ እየተመገቡ በአንድነት ፈጣሪን ማመስገኑ የተሻለ የቅድስና ህይዎት ነውና ወደ ጥንቱ ማንነታችን እንመለስ ።                  መልካም ሱባዔ

No comments:

Post a Comment