ሰዎች አንድን ነገር ብንሰርቅ ወይም በጉልበት መንትፈን ብንወስድ ሌሎች እንዳይወስዱብን እንደብቀዋለን፤ አሊያም በጥንቃቄ እንይዘዋለን፡፡ ወደ ሥልጣን ከወጣን በኋላም መልሰን ወደ ታች መውረድ እንፈራለን፡፡ ብንወርድ እንኳን ታጅበን እንሄዳለን፡፡ ጉዞአችንም ሁሉ በፍርሃት የተመላ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የተቀመጥንበት ወንበር ከመጀመርያውኑ የእኛ ሳይሆን ሌሎች ነበሩበትና፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባርያዎቹን መልክ ይዞ ከልዕልና ወደ ትሕትና ወረደ፡፡ ሲመጣም ብቻውን መጣ እንጂ በመላእክት ወይም በሌላ ጭፍራ አልተጠበቀም፡፡ ሰው ሆኖ ራሱን ባዶ ስላደረገም ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አላስቀረበትም፤ እንደ ተቀማም አልቆጠረውም፡፡ ማንም አይወስድበትና “የባርያዎቼን መልክ አልይዝም” ብሎም አልተከራከረም፡፡ የማዳን ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ዓለም ሳይፈጠር ከአባቱ ጋር በነበረው ክብር የሚቀመጥ አምላክ ነውና፡፡ ይህ ሥልጣኑ ድሮውንም የባሕርዩ ነውና ራሱን ዝቅ ዝቅ አደረገ፤ ለሞት ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘ ሆነ፡፡
ሞታችንን ለሞተልን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁንለት፤ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment