ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4
ዕንባ የተጀመረው በአዳምና በሔዋን ነው፡፡ ያለቀሱትም አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በልተው እግዚአብሔርን በመበደላቸው ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ የተጀመረው በንስሐ ነው፡፡ በቀሌምንጦስ «አልቦቱ ካልዕ ሕሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ፤ ለአዳም ስለ ኃጢአቱ ከማልቀስ /ኃጢአቱን እያሰበ ከማልቀስ/ በቀር ሌላ አሳብ /ግዳጅ/ አልነበረውም» ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ የዕንባ ቀዳሚ ጠቀሜታ ሰውን በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ተመዝግቧል፡፡ «ወበአንብዕየ አርሐስኩ ምስካብዬ፤ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ» የሚለው ቅዱስ ዳዊት የንስሐ ዕንባውን፣ የጸሎት ዕንባውን ነው፡፡ /መዝ 6÷6/ ጌታችንም በወንጌል «ብፁዓን እለ ይላህው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌስሑ፤ ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4/ ሲል ያስተማረው የሚገባው ለቅሶ ወይም ዕንባና ሐዘን የንስሐ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በሌላም ቦታ «እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፣ ታዘናላችሁና፣ ታለቅሱማላችሁ» /ሉቃ 6÷25/ ሲል ያስጠነቀቀን ጠቃሚውን ዕንባና ሐዘን ለማስተማር ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም «ከሳቅ ሐዘን ይሻላል፣ ከፊት ኀዘን የተነሣ ደስ ይሰኛልና፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት [በንስሐ] ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት [ኃጢአት በሚፈጸምበት ቦታ] ነው» በማለት የንስሐ ዕንባን መፈለግ ጠቢብነት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ከዚህም በላይ በቅድስና ሕይወት የሚኖሩ ቅዱሳን በዐሥሩ መዓርጋት ሲሸጋገሩ አራተኛው መዓርግ አንብዕ ይባላል፡፡ ይህም ፊታቸው ሳይከፋውና ሰውነታቸው ሳይሰቀቅ ዕንባን ከዓይናቸው ማፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ ይህን የመሰለ ጠቀሜታ ያለው በመንፈሳዊነትም የብቃት ደረጃ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment