ሁልጊዜ በስርዓተ ቅዳሴያችን ላይ የሚነገር አዋጅ ነው። በሰው ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነገር ነገር ብዙ ጊዜ ክብርና ቦታ አይሰጠውም ስለዚያም ይመስላል ብዙ ሰው ይህ አዋጅ ሲታወጅ የተለመደ ስለሆነ ብቻ የዲያቆኑ የአገልግሎት ድርሻ መሆኑን ከመገመት ያለፈ ቦታ የማንሰጠው።
በቤተክርስቲያናችን ስርዓት ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች በእናት ቅድስት ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የአገልግሎት ድርሻ አላቸው ። ምክንያቱም አገልግሎት የተፈጠረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን አገልግሎ በረከትን እንዲያገኝ ስለሆነ ሁሉም በአቅሙ የተሰጠው የአገልግሎት ድርሻ አለ።
ዲያቆኑ ተንስኡ ሲል ህዝቡ እግዚኦ ተሰሃለነ (አቤቱ ይቅር በለን ) ይላሉ። ካህኑ ሰላም ለኩልክሙ ሲል ህዝቡ ከመንፈስህ ጋራ (እንደቃልህ ይይደረግልን ) ይላሉ ።
እንደቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ካህኑ የጌታ ምሳሌ ሲሆን ዲያቆኑ የአዳም ሞዕመናን አምስት ሽ አምስት ሞቶ ዘመን በዲያቢሎስ ባርነት የነበሩ የአዳም ልጆች ምሳሌ ነው ።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእጸ መስቀል ላይ ተሰቅሎ አዳም በስህተት ያመጣውን ሞት በሞቱ ድል አድርጎ አዳምን ፍለጋ ወደ ሲኦል በወረደ ጊዜ ቀድሞ የሰጠውን ተስፋ ይጠብቅ የነበረው አዳም ቀኑ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ በሲኦል ሆኖ ለጸሎት ተነሱ የሚለውን አዋጅ አውጇል። ከዚያም በሲኦል የነበሩ የአዳም ልጆች አዋጁን ሰምተው አቤቱ ይቅር በለን ብለው ወደ አምላካቸው ልመና አቅርበዋል። ኃዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጻፈው ጌታ እንደተናገረው።
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። ዮሐ 15፥13 ባለው መሰረት የልጆቹን ጩኸት ሰምቶ ቸል የማይለው አምላክ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ብሎ በመካከላቸው ቆመ ዲያቢሎስና ሰራዊቱ ተጨነቁ አዳም ከነልጆቹ ነጻ ወጣ። ዛሬም የቤተክርስቲያን ልጆች በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በምትመሰለው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ልመናቸውን ያቀርባሉ ቸሩ አምላካችንም ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ብሎ በተናገረው መሰረት በቤቱ ተገኝተው ወደ እርሱ በጸሎት የሚቀርቡትን ይባርካቸዋል የልቦናቸውንም ሃሳብ ይፈጽምላቸዋል። አንዳንድ በአሁን ዘመን ያለን ክርስቲያኖች በትክክል ስለ ቤተክርስቲያናችን ስርዓትና ደንብ ካለማወቅ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በመዘንጋት ወደቤተክርስቲያን ስንሄድ ስለግል ጉዳያችን ብቻ ወደ እግዚአብሔር ልመና እናቀርባለን። እግዚአብሔር ደግሞ ከራስ ይልቅ ስለሌላው እንድንጸልይ ነው የሚፈልገው። በዚህ የተነሳ በጸሎታችን የምንጠይቀውን ነገር ሳናገኝ እንቀራለን። ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ያለችበትን ሁኔታ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ምንም እንኳን ቤተክርስቲያን ከፈተና ርቃ የማታውቅ ብትሆንም የአሁኑ የተለየ ነው። ምክንያቱም የውጭውን ፈተና ለመቋቋም በምትሮጥበት ጊዜ የውስጡ ፈተና እየባሰ በመሄዱ ምክንያት አህዛብ ሊያጠፏት አሰፍስፈዋል። አሁን በእጅጉ እያሰጋ ያለው በእኛ መካከል ያለው ልዩነት ነው። የአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች በተለያየ ጎራ ተሰልፈን የአህዛብና የመናፍቃን መቀለጃ መሆናችን በጣም ያሳዝናል። ቤተክርስቲያን መቸም ቢሆን በክርስቶስ ደም የከበረች ናትና ክብርዋ ለዘለዓለም ተከብሮ ይኖራል። እኛ ግን የዚች ቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ተብለን በእርሷ መክበር ሲገባን የዓለምን ሃሳብና ፍላጎት ይዘን በመምጣት እውነተኛ የሆኑትንም እስከማወክ ደረስን። ስለዚህ ያለፈው ዘመን ይብቃን እስቲ አሁን ደግሞ ያፈረስነውን የፍቅር ግንብ መልሰን ለመገንባት ለራሳችን ቃል እንግባ። ስለ ቤተክርስቲያን ሰላም እንጸልይ። ቢቻል ለመገንባት እንጣር እንጅ ከቤተክርስቲያን ጠላቶች ጎራ ተሰልፈን የእናታችንን ቤት ለማፍረስ አንሽቀዳደም። የሰላም አምላክ በምህረቱ ይመልከተን ። |
No comments:
Post a Comment