በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሁን እንዳለንበት የሚያሳፍር ታሪክ ይኖራል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ምክንያቱም የተማረው ካልተማረው በታች የሚያስብ ሆኖ ተገኝቷል። ባለጸጋው ከድሃው በታች ሲያለቅስ ታይቷል። በዳዩ ከተበዳዩ በላይ እሮሮ ሲያሰማ ታይቷል። መሪው ከተራው ህዝብ በላይ መብቴ ጎደለ ሲል ተሰምቷል። ሁሉ የተሰጠው በእጁ ያለውን ማጣጣም አቅቶት ሲያለቅስ ታይቷል። ይሉኝታ የሚባል ነገር ጠፍቶ ሁሉ ለኔ ይሁን ሌላው ግን ምንደኛ መሆን አለበት የሚል ሰው በኢትዮጵያ ምድር በጉልህ ታይቷል። ታዲያ እንደዚህ ዘመን ነውረኛና አሳፋሪ ጊዜ ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት አይከብድም?
በ1998 ዓ.ም. በጅማ በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተሠዉ ምእመን
የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ክፉ ባህርያት ተዘርተው፣ በቅለው፣ ተኮትኩተው፣ ለምልመው፣ አብበው እስኪያፈሩ ድረስ እያየየ እየሰማ ምናልባት በጎ ዘመን ይመጣ ይሆናል በማለት አብዛኛው ዝምታን መርጦ ኖሯል በመሆኑም ይሆናል ያለው ሳይሆን መሆን ያለበት ሆኖ ፍሬውን መብላት ግድ ሆኖበታል።
አሁንስ ምን ተማርን? እየተዘራ ያለው እስኪበቅል እንጠብቅ ወይስ ያለፈው ይብቃ ብለን ወደ ማስተዋል ተመልሰን ለትውልድ ከሚተላለፍ ደዌ ኢትዮጵያን እንታደግ? እሳቱም ውሃውም በእጃችን ነው። የሚጠቅመንን መምረጥ ከእኛ አልፎ ለልጆቻችን የሚተርፍ ሀገር እንዲኖረን ያስችላል።
የእኛ ትልቁ ችግር የሚጀምረው የተፈጥሮን ሥርዓት ባለመቀበል አንድ ሰው በተወለደበት ሥፍራ መጤ ነህ ከማለት ነው። እኔ ብቻ ልኑር የሚለው ፈሊጥ ሰይጣናዊ ከመሆኑም በላይ ሞትን ወደ ራስ መጋበዝ ነው። እኔ ልኑር ስል ሌላውም ለመኖር የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ካልተገነዘብኩ እንደ እኔ ያለ ጭፍን ከየት ይገኛል? ከዚህም በላይ ደግሞ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለው የሰይጣን ፈረስ ሁኗል ማለት ነው። ቃየል ወንድሙን አቤልን በጥቅም በመግደሉ የሰይጣን ወንድም ተብሏል ዘፍ 4፥8
No comments:
Post a Comment