Wednesday, March 6, 2019

የድሃዋ እንባ መዘዝ

ህዝበ እስራኤል በግብጽ ስደት በነበሩበት ዘመን የደረሰባቸው መከራ እጅግ የከፋ እንደነበር በኦሪት ዘጸአት ምእራፍ 1፥8 ጀምሮ ያለውን ታሪክ ስናነብ በሰፊው እንረዳለን። ምንም እንኳን በስደት በሰው ሀገር የሚኖሩ ቢሆንም እንደሰው ሊሰጣቸው የሚገባውን ክብር በማጣታቸው የመከራ ኑሮ ይኖሩ ነበር። ሰው በሰውነቱ የትም ቢሆን ክብር ሊሰጠዉ ይገባል። ወደ ታሪኩ ስንመለስ እንደ ሰው ሰርቶ መብላት፣ ቀን ሰርቶ ሌሊት ማረፍ፣ ወልዶ መሳም፣ ሰርቶ የድካምን ዋጋ ማግኘትወ ዘ ተ አይፈቀድላቸውም ነበር። ዛሬ በእኛም ሀገር ይህ ሲፈጸም በተደጋጋሚ አይተናል። በእስራኤላውያን ላይ ይህ ግፍ ሊደርስ የቻለው አስቀድሞ ለምድረ ግብጽ መልካም ያደረገ እስራኤላዊ ዮሴፍን የማያውቅ ንጉስ በመነሳቱ ነበር። ክፉና ጠማማ ሰው ደግነትን ቢያውቃትም የበጎ ነገር ጠላት መሆኑ የተለመደ ነው። ዛሬ በየክፍለ ሀገሩ ሰዎች እየተፈናቀሉ ያለው በጎው ነገር ጠፍቶ ሳይሆን የበጎውን ዘመን ሰዎች ታሪክ መዘከር ስለማይፈለግ ነው። እስራኤላውያን ችግራቸውን የሚመለከት ዳኛ በማጣታቸው አምርረው አለቀሱ። የለቅሷቸው መጠን ምን ያክል እንደሆነ ለመረዳት በፈርኦን ላይ የመጣውን መአት አይቶ መረዳት ይቻላል። ዛሬም በሞኝነት አይናችሁ ታውሮ የድሆችን እንባ ቸል የምትሉ ነገ ጎርፍ ሆኖ እናንተንና የኔ የምትሉትን ያሰጥማችኋልና አስቡበት።





ከእሥራኤላውያን ታሪክ አንዱን እናስታውስ; በምድረ ግብጽ ተወልዳ በዚያው የምትኖር፣ የአባትና የእናቷን ሀገር የማታውቅ አንድ ሴት ነበረች። የመከራ እንጀራ ከሚበሉ ወገኖቿ ጋር በውርደት ትኖር ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ መከራ ተጭኗቸው ብታይም ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ በሰማይ በክብሩ እንደሚኖር ታምን ነበር። የባርነት ኑሮ ስብእናዋን አቀጭጮ ልቧን ሀዘን ቢሰብረውም በማህፀኗ ሁለት ልጆችን አርግዛ የመውለጃዋን ቀን ትጠባበቅ ነበር። የግብጽ ሹማምንት ለፈርኦን እጅ መንሻ የሚያቀርቡት ፒራሚድ እያስገነቡ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በስደተኞቹ በእስራኤላውያን ገልበት ነበር። የጉልበት ሥራ ለመስራት ከሌሎች ወገኖቿ ጋር ደፋ ቀና እያለች ኑሮዋን ትገፋ ነበር። ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እንዲሉ ድንጋይ መፍለጥና መሸከም፣ ጭቃ መርገጥ ወዘተ የለመደችው ተግባር ነው። አንድ ቀን ግን እንዳለመደችው የእለት ተግባሯን ለማለማከናወን አቅም አነሳት። የምትደገፈው ፈለገች አላገኘችም። ስራው ፋታ የሚሰጥ አይደለምና።

የመውለጃዋ ወቅት በመድረሱ ከቆመችበት ረግረግ ወጥታ ልጆቿን ትገላገል ዘንድ ኃላፊውን ፈቃድ ጠየቀች ነገር ግን መልሱ ልብ የሚሰብር ነበር። እየተሳለቀ እንዲህ አላት " የሰው ደም ጭቃውን ያጠነክረዋልና እዚያው መውለድ ትችያለሽ ስራሽን ማቋረጥ አትችይም"። መንታ ልጆችን በዚያ በጭቃው ላይ ወለደች ደሟ እንደ ውሃ ፈሰሰ፣ ዘጠኝ ወር ተሸክማ በእንክብካቤ ያኖረቻቸውን ልጆቿን ከጭቃው ላይ በእግሯ ረገጠቻቸው።ሀዘኗ እጅግ በረታ፣ እንባዋ እንደ ውሃ ፈሰሰ፣ ከሰው ወገን የሚረዳትም ሆነ እንባዋን አይቶ የሚያዝንላት አጣች። የዚህን ጊዜ የመጨረሻ ጉልበቷን ተጠቅማ ከአይኗ የሚፈሰውን እንባ በእጇ አቁራ ወደ ሰማይ እረጨችው " እውነት በዚህ ሰማይ ላይ የአባቶቻችን አምላክ አለህን? ብላ በምሬት ጮኽች። ያ ድምጽ እንደ ወትሮው ያለ አልነበረም፣ ያ እንባ እንደ ቀድሞው አልነበረም። ከአንጀት ፈንቅሎ የወጣ በደም የታጀበ እንባ ነበር።  የታመነችው አምላክ ዝምታውን ሰበረ ወደ ሙሴ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ። "በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ"ዘጸ 3፥7

ሙሴ ወደ ጨካኙ ንጉስ ወደ ፈርኦን ተላከ። እግዚአብሔር ህዝቤን ልቀቅ ብሎሃል አለው እምቢ አለ። የተለያዩ ተአምራትን አሳይቶ ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን ነገረው ነገር ግን በበደል ላይ በደል አበዛ። በመጨረሻም በዚያች ምድር የፈሰሰው እንባ ከንቱ እንዳይደለ ዓለም ያውቅ ዘንድ ፈርኦንን ከነሰራዊቱ በባህር አስጥሞታል። 

የድሆችን እንባ እግዚአብሔር ይሰማል። ድሆችን ማሰቃየት ከእግዚአብሔር ጋር መታገል ነው። ብዙዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገሉ ተሰብረዋል።  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል"እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም" መክ 4፥1
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፈው ለዓለም ህዝብ የሚጨነቁ መሪዎች እንደነበሯት ታሪክ ምስክር ነው። ዛሬ ግን ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ ከእግዚአብሔር የተላኩ የተባሉት ሳይቀር መንደርተኛ ሆነው በማየታችን ተስፋቢስ ሆነናል። ለህዝብ መብት እንቆማለን የሚሉ ብዙ አሉ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በረት አልባ መንጋዎች ሆነው እያየን ነው። 
ህዝብን ለመምራት ከፊት ያላችሁ ወገኖች ምክር የምትሰሙ ከሆነ የድሆችን እንባ አትናቁ። ከእናንተ አልፎ ለትውልድ የሚተርፍ የመከራ እዳ አታኑሩ።

በየእለቱ የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን እናቶችን ባሰብኩ ጊዚ ይህ ጥቅስ ትዝ አለኝ" እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፤ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል"። መክ 4፥1


1 comment: