የሰው ሃሳብና የእግዚአብሔር መንገድ የተራራቁ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ የምንጠብቀው ሳይሆን ያልተገመተው ሲሆን ማየት የተለመደ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን አድራጊ በመሆኑ የሚሳነው የለም ነገር ግን ሁሉን የሚያደርግበት ጊዜ አለው። ዛሬ ላይ ሆኘ ምነው አሁን እያየንና እየሰማን ያለነው ነገር ከጥቂት ዓመታት በፊት ሆኖ ቢሆን ለማለት አሰብኩና የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አለማስተዋል ነው ብየ እራሴን ወቀስኩ። ያለፈው ኃዘን ባይኖር የዛሬው ደስታ የለም። ትላንት መስዋእት የሆኑ ሰዎች ባይኖሩ የዛሬው ሰላም ትልቅ ቦታ አይሰጠውም ነበር። ሁልጊዜም አንዱ እየቀለጠ ለብዙዎች ማብራቱ የተለመደ ነው። ለለወደፊቱ አንዱ እየሞተ ሌላው የሚኖርባት ሀገር እንዳትኖረን በጋራ ማሰብ አለብን።
ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የሰላም መልእክት በሀገራችን እየጎረፈ ነው። ይህ የሰላም መልእክት የናፈቀው ህዝብ ሰላምን መስበክ ከናፈቀው መሪ ጋር ሲገናኝ ሰኔና ሰኞ ሆነ ማለት ይህ አይደል? አሁን እየታየ ያለውን የሰላም መንፈስ በቁመተ ሥጋ ሆነው ሳያዩ ላለፉ ወገኖች እጅግ እናዝናለን። የሰላም መንገድ ተሰውራ ብዙዎች አጥፊ ብዙዎች ተጎጅ ሆነው አልፈዋል። ማለፍ የማይቀር ቢሆንም ሰላምን አጥቶ ማለፍ ለየትኛውም ወገን ቢሆን አሳዛኝ ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት" "፤ ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም። " (መዝ 34: 14) እንዳለው ሰላምን ከሁሉ አስቀድሞ መፈለግ ይገባል። አሁንም ለኛ የሚሆን ብዙ ሰላም አለ። ብዙ በረከት የሚገኝበት ሰላም በፍቅርና በመተሳሰብ የሚመጣ በመሆኑ ያለፈውን ክፉ ሃሳብ አስወግደን ወደ ፍቅር እንምጣ። ባለፈው ብዙዎችን አጥተናል ከዚያም አልፎ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ስለነበር ብዙ ተጨንቀን ነበር። ካጣነው ሁሉ በላይ የሀገር መኖር ከሁሉ ይበልጣልና እግዚአብሔር ይመስገን። ከሰላም እርቀን በነበርንበት ዘመን ያጣነውን ነገር በገንዘብ መተመን አይቻልም። የሰው ህይዎት በገንዘብ አይተመንምና።