ከፍጥረታት ሁሉ አወቂና ክቡር ሆኖ የተፈጠረ እንደ ሰው ያለ ፍጡር አልተገኘም። ይህን ክቡርና አዋቂ የሆነ ፍጡር ለመምራት በእውቀትም ሆነ በችሎታ ልቆ መገኘት ይጠይቃል። ከስነፍጥረት ጀምሮ ያለውን ታሪክ ስናነብ መሪዎች ነበሩ። ምንም እግዚአብሔር መርጦ መሪ ቢያደርጋቸውም በአስተሳሰባቸው ከሚመሩት ህዝብ በታች ሆነው በመገኘታቸው ፍጻሜያቸው ያላማረ ብዙዎች ናቸው። ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻል ነበር ነገር ግን በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልግባ።
የተነሳንበት ርእስ የተለያዩ ትርጉሞች ሊሰጥ የሚችል ቃል ስለሆነ በማጥበቅና በማላላት እንዲሁም በመተርጎም ፍሬ ሃሳቡን ማግኘት እንችላለን። ስናጠብቀው ሁሉ የሚሰማው, ሁሉ እሽ በጄ የሚለው እንዲሁም የሚደመጥ ወ ዘ ተ ማለት ሲሆን ስናላላው ደግሞ የሚሰማ,የሚያዳምጥ, ለሃሳቦች ቦታ የሚሰጥ ወ ዘ ተ ልንለው እንችላለን።