
ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከመገሰጹ በፊት ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ በእስራት ላይ ያሉ አህያና ውርንጭላዋን ፈትተው እንዲያመጡ አዞ ነበር። አትፍቱ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ የሚል መመሪያም ሰጥቷቸው ነበር። የሰው ልጆችን ሁሉ ከእስራት ሊፈታ እንደመጣ ሲያጠይቅ ይህን ተናገረ። ለምን ትፈታላችሁ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው። እነሱም እንደታዘዙት ለጌታ ያስፈልጉታል ብለው ፈትተው አምጥተውለታል። ቃሉም እንዲህ ይነበባል " ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ፦ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ማቴ 21፥1"