Friday, February 14, 2014

እስከ መቼ?

ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ስጦታዎች ትልቁ ሃይማኖት ነው። ሰው ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ ክብር እንዳለውም የታወቀው በሃይማኖት ኖሮ ከፈጣሪው ጋር ስለሚገናኝ ነው። ታዲያ ይህን ትልቅ ጸጋ አክብሮና ጠብቆ የመኖር ኃላፊነት አለበት። ቅዱሳን እራሳቸውን ለእግዚአብሔር በማስገዛታቸው በዚህ መንገድ ተጉዘው ወደ ዘለዓለም እረፍት እንዲገቡ እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ <<  ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ይሁዳ 1፥3 >>  ያለው። የሰው ልጆች  በጸጋ የእግዚአብሔር  ልጅነትን ስላገኙ በሃይማኖት ኖረው ያባታቸውን  የእግዚአብሔርን ርስት እንዲወርሱ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነው።
 
ሃገራችን ኢትዮጵያ የቅዱሳን ሃገር በመሆኗ ህዝቦቿም በአምልኮተ እግዚአብሔር ለብዙ ዘመናት ጸንተው የኖሩ በመሆናቸው ብዙ ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ወደ ሃገራችን እየፈለሱ እንደመጡ በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጽፎ እናገኛለን። ዛሬም ቢሆን በዓለም የሚገኙ የታሪክ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መጘኛ፣ የታሪክ ማህደር መሆኗን እየመሰከሩ ነው። ድንቅ ሃይማኖታዊ ስርዓቷንና ትውፊቷን ለማድነቅ በየእለቱ ብዙ የዓለም ህዝቦች እየጎረፉ ነው።  በኢትዮጵያውያን በኩል የሚታየው ግን  ብዙ ደስ የሚል አይደለም። በተለያየ አቅጣጫ ህዝቡ እየተፈተነ  ነው።  በጎ ምግባርንና ሃይማኖትን የተማረው ከሃይማኖት አባቶቹ ነበር ። ዛሬ ላይ በአባቶቹ ተስፋ በመቁረጥ እምነቱ እየተሸረሸረ በመምጣቱ አህዛቡንም ሆነ መናፍቃኑን መቋቋም አቅቶት በእነሱ እየተማረከ የክፉ ስራቸው ተባባሪ በመሆን ቤተክርስቲያኑንና ሃገሩን ታሪክ አልባ እያደረጋት ነው። 


ለመግቢያ ያክል ይህን ካልኩ አንዲቱ ቅድስት ቤተክርስቲያን በአሁን ሰዓት በሰዎች ስንኩል ሃሳብ ምክንያት ልጆቿ ተከፋፍለው በሚያሳፍር ሁኔታ ላይ ትጘኛለች። በተለይም በዓለም ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባት በምድረ አሜሪካ ያለው የቤተክርስቲያን ክፍፍል ስር እየሰደደ በመምጣቱ ወደፊት ለትውልድ መጥፎ አሻራ እየጣለ በመሄድ ላይ ይገኛል። ምናልባት በሰዎች ምክንያት የመጣ ይሆናል ስለዚህ ሰዎች ያልፋሉ ያን ጊዜ ይስተካከላል የሚል ተስፋ ያላቸው ብዙዎች ነበሩ። ነገር ግን ሰዎች አለፉ ዘርተውት የሄዱት የመለያየት መንፈስ ግን የሚያልፍ አልሆነም። በአባቶች በኩል ስለሰላሙ ያለው ትጋት በጣም የወረደ መሆኑ በጣም አደገኛ ሁኔታ ላይ እንዳለን ያሳያል። ብዙዎቻችን የምንናፍቀው ሰላም መቼ ነው የሚመጣው?
እያሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ ነገር ግን መልስ የሚሰጥ የለም። ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም እንደተባለው ሁሉም ዝም ብሎ ቀን እየገፋ ነው። ግን እስከ መቼ?  የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ በየጊዜው በሚወለዱ ክስተቶች ዶግማዊ ቀኖናዋ ሥርዓቷ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡ ይህን ሁሉም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ማወቅና ማክበር፣ መጠበቅ ማስጠበቅ አለባቸው። እንዲሁም ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉ እንዲያውቅ የቤተክርስቲያን አባቶች ግዴታ አለባቸው። ትውልዱ ይህን በደንብ ባለመረዳቱ ምክንያት አሁን ለደረስንበት ችግር አይነተኛ ምክንያት ሆኗል።
 
በምድረ አሜሪካ ያለውን መከፋፈል በጥቂቱ እንመልከት>   1, በኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ እንመራለን የሚሉ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ  የቤተክርስቲያናችን የበላይ አካል በመሆኑ የሚያወጣውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መቀበል አለብን( ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም ለምሳሌ 1,ወጭና ገቢያቸውን አያስመዘግቡም ፐርሰንትም አይከፍሉም 2, አገልጋዮችን በራሳቸው መስፈርት ነው የሚቀጥሩት 3, ቃለ አዋዲው በትክክል አይተገበርም ወ ዘ ,ተ ) የቅዱድ ሲኖዶስ አባላት ብፁአን አባቶች ለቡራኬም ሆነ ለአገልግሎት በሚመጡ ጊዜ አክብረን መቀበል ይኖርብናል። ቅዱድ ፓትርያርኩም ሆነ የሃገረስብከቱ ሊቀጳጳስ ዘወትር በጸሎት መታሰብ አለባቸው። የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበር መሆን አለበት። ከቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ጀምሮ የሚገኙት በህዝብ የተመረጡ የኮሚቴ አባላት መጠሪያ   ቦርድ ሳይሆን ሰበካ ጉባኤ መባል አለበት። ቤተክርስቲያን በመንግስትም ሆነ በአሁኑ ወቅት በሚገኙት ጳጳሳት የምትለካ አይደለችም። ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚወርደውን መመሪያ የማይቀበል ካህንም ሆነ ምዕመን በአንዲት ቤተክርስቲያን አምናለሁ ማለት አይችልም። በተለይ አገልጋዮች ካህናትና ዲያቆናት ከሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ውጭ ከሆኑ ክህነታቸው ይሻራል። ምክንያቱም ክህነታቸው የተገኘው ከሊቀጳጳሱ ስለሆነ ትዕዛዙን አልቀበልም ቢሉ የመሻር ስልጣን አለው። ወ ዘ ተ
 
2, ገለልተኛ>  ቤተክርስቲያኒቱን የሚመራው ካህንም ይሁን ምዕመን በህዝቡ ከሚመረጡት የቦርድ አባላት መካከል ይሆናል።በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት  አሁን ላለችበት ደረጃ ደርሳለች። ስለዚህ ተጠያቂዎች እነሱ ናቸው።  በኢትዮጵያም  ሆነ በአሜሪካ ያሉት አባቶች የተለያዩት በስልጣን አለመግባባት እንጅ ለቤተክርስቲያን ብለው አይደለም። ስለዚህ የሁለቱንም አቋም አንደግፍም። ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ  መንፈስ ቅዱስን ደግሞ ሰዎች እንደፍላጎታቸው ወደ ፈለጉት ቦታ መምራት አይችሉም ። ስለዚህ ለኢትዮጵያ የተሰጠው ይህ ትልቅ ጸጋ ሰዎች በስልጣን ስላልተግባቡ ወይም ከስልጣን ስለተወገዱ  ከሰዎች ጋር የሚሰደድ አይደለም ። ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ኢትዮጵያ ነው ያለው ብለን እናምናለን። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት መስመር እስኪይዝ ድረስ ከሁለቱም አካላት ጋር በአስተዳደር  ገለልተኛ ሆነናል። ለቡራኬም ሆነ ለአገልግሎት ብጹአን አባቶች ሲፈለጉ በካህናቱና በምዕመናኑ ተቀባይነት ያላቸው ኢትዮጵያ ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ብጹዓን አባቶች መጥተው ይባርካሉ። ክህነት ይሰጣሉ። የህዝቡን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል የፓትርያርኩና የሊቀጳጳሱ ስም ለጊዜው አይጠራም  በኢትዮጵያ የሚገኙት አባቶችም ሆነ በአሜሪካ የሚገኙት አባቶች በኢትዮጵያ  ከመንግስት  ጋር በውጭው ዓለም ደግሞ ከፖለቲከኞች ጋር ተስማምቶ መኖርን እንጅ በጉልህ የሚታዩ ስህተቶችን እንደ አባት ማረም አልቻሉም ። የህዝቡን አንድነት ለማስጠበቅ የጎላ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። ለህዝቡ ዴንታ የላቸውም። የቤተክርስቲያን ጉዳይ አያስጨንቃቸውም። ስለዚህ ወደፊት ለመንጋው የሚራሩ ከስህተት የጸዱ አባቶችን እስክናገኝ ወይንም አሁን በሁለት ጎራ የተከፈሉት አባቶች እርቅ አውርደው የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ለማስጠበቅ አንድ አቋም እስኪይዙ ድረስ ገለልተኝነትን መርጠናል። ወ ዘ ተ
 
3, ሲኖዶስ ተሰዷል የሚሉት > በኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ህገወጥ ነው። እውነታኛው ሲኖዶስ በስደት ነው ያለው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ናቸው። በኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ከመንግስት መመሪያ እየተቀበለ ነው። የሚሰራው። ( ነገር ግን እነሱም አንዳንድ ጊዜ የተቀዋሚ ፖለቲከኞችን ሃሳብ ሲ,ደግፉ ይታያሉ)  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በመንግስት ግፊት ነው ከስልጣን የተወገዱት።
ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት አለ ብለን አናምንም። ቀኖና ቤተክርስቲያን ተጥሷል። አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እስካልተመለሱ ድረስ ከያዝነው አቋም አንመለስም። ለዚህ ችግር ያደረሰን የኢትዮጵያ መንግስት ስለሆነ  እሱንም እንቃወማለን ወ ዘ ተ
 
4, ከሁሉም የሌሉ ነገር ግን በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን የሚያምኑ> የነዚህኞቹ ሃሳብ ከሌሎቹ ይለያል። ሁልጊዜ የሚያስጨንቃቸው የአባቶች እርቅና ሰላም ነው። በማንም ላይ መፍረድ አይፈልጉም። ይልቁንም በነሱ ኃጢአትና በደል ይህ ሁሉ እንደሆነ እራሳቸውን በመውቀስ ይናገራሉ። በአባቶች በኩል ለእርቅ የሚቀርበውን ቅድመ ሁኔታ እጅግ በመረረ ሃዘን ነው የሚሰሙት። ሁል ጊዜ በቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሰፍኖ ማየት የዘወትር ህልማቸው ነው። ሁላችን የአንድ አባት ልጆች ነን የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ደጋግሞ ከአንደበታቸው ሲወጣ ይሰማል። ለሁሉም አባቶች ጸሎት ቢደረግ ፈቃዳቸው ነው። ለመንግስት አካላትም ሆነ ለቤተክርስቲያን አባቶች ጸሎት ይደረግ ዘንድ ያሳስባሉ ነገር ግን የተለያየ ስም ይሰጣቸዋል።

ሁሉም ሊገነዘበው እና አንድ ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር አለ። ቤተክርስቲያን አንዲት ነች፣ ቤተክርስቲያን ቅድስት ነች፣ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ነች። በሰው ሃሳብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ የተገኘች ነች። ብዙ ቅዱሳን ደማቸውን ያፈሰሱላት አጥንታቸውን የከሰከሱላት ነች። ለብዙ ዘመናት አንድነቷ፣ ቅድስናዋ፣ ሐዋርያዊትነቷ ተጠብቆ ኖሯል። ዛሬ ላይ የነዚያን ቅዱሳን ህይዎት የማናውቅ ትውልዶች ብንነሳም። ክብሯ ዘለዓለማዊ ስለሆነ ትኖራለች። ግን ለምን ክብርት የሆነችውን ቤተክርስቲያን አክብረን፣ አስከብረን ፣ ከብረን መኖር አቃተን? እውነት በዚህ ዘመን ከቤተክርስቲያን የሚበልጥ የግል ጥቅም አግኝተን ነው? በተለይ ይህ የሚመለከተን ብናስተውል መልካም ነው። ህዝቡ ግራ እየተጋባ ነው። ትላንት በትንሽ ነገር የተጀመረው ዛሬ አቅጣጫውን ስቶ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው። በተለይ ብጹዓን አባቶች ምናልባት ከላይ በመሆናችሁ ከታች ያለው ምዕመን እየደረሰበት ያለውን የሞራል ውድቀት ለማየት ተቸግራችሁ ይሆናል። እስቲ ዘንበል የሚል አንገት ይኑራችሁ? በእናንተ የተነሳ ስንቱ ነው ጥርጥር ውስጥ እየገባ ያለው?  እውነት ይህ መረጃ ሳይደርሳችሁ ቀርቶ ነው? በተለይ በዚህ በአሜሪካ በየሳምንቱ በእለተ ሰንበት ሰላማዊ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወንባቸው አብያተክርስቲያናት ጥቂቶች ናቸው ። በሳምንት አንድ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ተገናኝተን እንሔዳለን ብለው ተስፋ የሚያደርጉ ምዕመናን ይህን ተስፋቸውን እያጡት ነው። የአጵሎስ የጳውሎስ በሚል ሁከት ማንሳት የተለመደ ሆኗል። ይህ ሁሉ መነሻው የአባቶች መለያየት ነው።
 
 በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያለው ህዝበ ክርስቲያን በአባቶቹ ተስፋ እየቆረጠ ነው። ሁልጊዜ የሚሰማው የሚያሳፍርና አንገት የሚያስደፋ ነው። ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነትና እድገት እናመጣለን ብለው የሚነሱ እንደወንጀለኛ የሚቆጠሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ግን እስከ መቼ?
 
እስከ መቼ የሚለው ጥያቄ የብዙዎቻችን እንደሚሆን እገምታለሁ። ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን መንፈሳዊ ሰው የሚታወቀው በፍሬው ነው። ጌታ በማቴዎስ ወንጌል ም 7 ቁ 13 እንዲህ ብሏል በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ይላል ስለዚህ እንደቃሉ ብንጓዝ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ክብር ይጨመርልናል እንጅ የሚጎድልብን ነገር አይኖርም።

በዓለም ላይ ብዙ ፈተና እና ችግር በየጊዜው የሚደርስባቸው አብያተክርስቲያናት አሉ ከነዚህም መካከል የግብጽ ቤተክርስቲያን አንዷ ነች። በየጊዜው በአህዛብ ፈተና ይደርስባታል። ነገር ግን ያንን ሁሉ ፈተና ተቋቁማ ዶግማዋንና ስርዓቷን ጠብቃ ትኖራለች። በዓለም ውስጥ ብዙ ገዳማትንና አብያተክርስቲያናትን እየመሰረተች ትገኛለች። አገልጋዮቿም ሆኑ ምዕመናኗ ፍቅራቸውንና አንድነታቸውን አጽንተው ይኖራሉ። መቸም ለኛ ከነሱ የቀረበ የለም ፥ ብዙ መጻህፍትን ከነሱ እየወሰድን አስተርጉመን እየተጠቀምን ነው። መጻህፍቱን ብቻ ሳይሆን በየዘመኑ ትውልዱን የሚያንጹበትን ከላይ እስከታች የተዘረጋ የማይናወጽ ጽኑዕ መዋቅራቸውንም መውሰድ ያለብን ይመስለኛል።  መፍትሔ ስለሚያገኙለት እንጅ በየዘመኑ ፈተና ሳይገጥማቸው ቀርቶ አይደለም።  ከነሱ ተምረን በመካከላችን የገባውን እንክርዳድ  አስወግደን ንጽሂት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ለዓለም ምሳሌ እንድትሆን ማድረግ ይጠበቅብናል።  
 
 

1 comment:

  1. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ በየጊዜው በሚወለዱ ክስተቶች ዶግማዊ ቀኖናዋ ሥርዓቷ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡

    ReplyDelete