ሰውና እንስሳ ከሚለዩባቸው ነገሮች አንዱና ዋናው ነገር የሰው ልጅ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን ለይቶ ማወቅ መቻሉ ሲሆን እንስሳት ግን ይህን የሚያውቁበት አእምሮ ስለሌላቸው በሰው ፈቃድና ፍላጎት ስር መሆናቸው ነው። ብዙ ጊዜ ረጋ ብሎ የሰሩት ነገር ፍሬያማ ይሆናል። የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል አደል የተባለው፥ ቀደም ሲል የነበሩት አባቶቻችን ሃገር ሲመሩ፣ ቤተክርስቲያንን ሲመሩ፣ ቤተሰብን ሲመሩ ቆም ብሎ የማሰብ ትልቅ ጸጋ ነበራቸው። ለዚያ ነው ዛሬም ድረስ ያ አሻራ ለትውልድ ተላልፎ ወደ ስህተት የሚጓዝን ሰው ቆም ብለህ አስብ ፣ ቆም ብለሽ አስቢ፣ ቆም ብላችሁ አስቡ እየተባለ በምሳሌ የሚነገረው።
አባቶቻችን በተግባር ነበር የሚያሳዩት እኛ ግን በአንደበታችን እንኳን ለመናገር እየከበደን ሰዎች ስህተት ውስጥ ሲገቡ እያየን ዝም እያልን ነው። ቆም ብሎ ማሰብ ለማንኛውም ሰው አስፈላጊ ነው። ሃገር ለሚመሩት፣ ቤተክርስቲያንን ለሚመሩት፣ ቤተሰብን ለሚመሩት፣ በትዳር አንድ ሆነው ለሚኖሩት፣ በስራ ጉዳይ ተገናኝተው አብረው ለሚኖሩት ወ ዘ ተ ። ቆም ብሎ ማሰብ ከሌለ ሃገርም ሰላም አትሆንም ቤተክርስቲያንም የሰማይ ደጅ መሆኗ ቀርቶ የገሃነም ደጆች የከበቧት እንቅብ የተደፋባት የፋኖስ መብራት ነው የምትሆነው። በትዳር ህይዎት ያሉ ሰዎችም እንዲሁ ቆም ብለው የሚያስቡበት ጊዜ ከሌላቸው በሰላም ይኖር የነበረው ቤተሰብ መበታተኑ የማይቀር ነው። እስቲ ወገኖች እንመካከር፥ እውነት በኑሯችን ቆም ብሎ ማሰብ የሚባለው ነገር አለ? ካለ መልካም። ከሌለ ግን ሊኖር ይገባዋል።
ዛሬ ያለው ትውልድ ሁሉን ባንድ ጊዜ ማድረግ የሚፈልግ ነው። ነገር ግን ለሰው የተሰጠው ጸጋ እንዲህ አይደለም። ሁሉን የሚያደርግበት ጊዜና ወቅት ተሰጥቶታል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ጊዜ አለው ይለናል
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። መክ 3፥1
ይህም ማለት ቆም ብሎ እያሰበ እንዲሰራ ማለት ነው። እየሮጡ ማሰብ አይገባም። እየጮኹም ማሰብ አይቻልም። አስቀድሞ ወዴት ነው የምሮጠው፣ ለምንድነው የምሮጠው። እስከየት ድረስ ነው የምሮጠው ? ወደማነው የምጮኸው? ለምንድነው የምጮኸው? ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ዝም ብሎ በመሮጥ ሜዳሊያ አይገኝም። ብዙ በመጮህም ልንሰማ አንችልም። በአግባቡ መጮህ ነው መልስ የሚያስገኘው። ለዚያ ይመስለኛል በምንደክምበት ነገር ሁሉ ውጤታማ የማንሆነው።በዓለማችን 24 ሰዓት እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ህዝብ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት። ታዲያ ለምንድነው የጸሎታችን መልስ የሚዘገየው? በብዙ መልኩ እንጮኻለን ግን አልተሰማንም ለምን ቢባል ቆም ብሎ ማሰብ። ጎጅ ባህል እየሆነ ስለመጣ ነው።
ቤተክርስቲያንን የሚመሩት አባቶቻችን በተለያየ መንገድ ስንፈልጋቸው በስራ ተወጥረው ነው የምናያቸው። ነገር ግን የህዝቡን ጥያቄ መመለስ አልቻሉም ። ለምን ስንል ቆም ብለው እያሰቡ ስለማይጓዙ። ሃገር የሚመሩትም እንዲሁ። ከሁሉ በፊት መሪ ማለት ምን ማለት ነው? ከሁሉ መርጦ እኔን ለምን መሪ አደረገኝ? ከኔ በፊት በኔ ወንበር ላይ የተቀመጡ እንዴት ነበር ህዝብን የሚመሩት? ስለምን ነበር ህዝብ የልብሳቸውን ጫፍ ለመንካት ይጓጓ የነበረው? እኔን ለምን ህዝብ ጠላኝ? ከነሱ በምንድነው የተለየሁት? ቆም ብለን ስናስብ እነዚህን ጥያቄዎች እራሳችንን ጠይቀን መልሱም እኛውጋ እንደሆነ ለመረዳት እንችላለን።
ብዙ ባለ ትዳሮች ብዙ ደክመው የገነቡትን ትዳር በቅጽበት ሲያፈርሱት ይታያሉ። ቆም ብለው ቢያስቡ ግን ወደ ስህተት እንጅ ወደ እውነት እየሄዱ እንዳልሆነ ይረዱት ነበር።
አሜሪካን ሃገር የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩት የምንሰማው ነገር አለ። ኢትዮጵያ እያሉ ስለነበራቸው ቪላ ቤት፣ ስለነበራቸው የቤት ሰራተኛ፣ ስለነበራቸው ስልጣን ወ ዘ ተ ነገር ግን አሜሪካ መጥተው ዝቅተኛ ስራ እንደሚሰሩ፣ ምግብ አብስለው እንደሚመገቡ፣ ይህ ሁሉ በሃገር ቤት እንዳልነበረ ያወራሉ። እውነት ነው በሃገራቸው ተከብረውና ተንደላቀው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ዝቅ ብለው እንደሚኖሩ ይታወቃል ። ወደ እውነቱ ስንመጣ ግን እነዚህ ሰዎች አሜሪካ ከኢትዮጵያ ትሻላለች የሚል ግምት እንጅ ለኔ ከኢትዮጵያ አሜሪካ የተሻለ ኑሮ እኖራለሁ ብለው ቆም ብለው ለማሰብ አልቻሉም ነበር ማለት ነው። የቆጡን ማውረዳቸው እንጅ በጉያቸው ስላለው የሚያስቡበት ጊዜ አልነበራቸውም። ቀድሞ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ነው ያለው የሃገሬ ሰው? በዚህ ርዕስ ስር ብዙ ማለት እንችላለን ። የመልእክቱ ዋናው ዓላማ እየተረሳ ያለውን ነገር ለማስታዎስ ስለሆነ ከዚህ በላይ ብዙ መጻፍ ለማንበብ አድካሚ እንዳይሆን እዚህ ላይ ይበቃኛል። ቆም ብለን ልናስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉን። አሁንም ጊዜ አለን ቆም ብለን ማሰብ ከቻልን ሁሉም ይስተካከላል። ይህን ያላደረግን እንደሆነ ግን በእግዚአብሔር ላይ እንዳመጽን ነው የሚቆጠረው። በእግዚአብሔር ላይ ያመጹ ደግሞ መጨረሻቸው ጥፋት ነው። ስለዚህ ከጥፋት ለመዳን << ለዘሃለፈ ስርየት ወለዘይመጽዕ እቅበት >> ይቅር በለን ማለት ያስፈልጋል። ቆም ብሎ ማሰብ //
kale hiwot yasemalen kesis
ReplyDelete