Thursday, June 28, 2012

ምን እያለምን ነው?

በተለያዩ ዘመናት ራእይ አልባ ትውልዶች እንደነበሩ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ራእይ አልባ የሚባሉት ነገን አስበው ዛሬ መልካም ነገር ለማድረግ የማይተጉ። ወይንም ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ነገን ተስፋ አድርገው በመኖር በመከራ የማይታገሱ ናቸው። ለምሳሌ በሎጥ ዘመን የነበሩትን ትውልዶች ብንመለከት በሰዶም ከተማ ያሉ በሙሉ ከሊቅ እስከደቂቅ በኃጢአት የተጨማለቁ ነበሩ። በመሆኑም ለነገ የሚተርፍ አንዳችም መልካም ስራ የሰሩት ስለሌለ ፍጻሜያቸው ጥፋት ሆነ። ለጊዜው እነሱን አነሳን እንጅ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ከነሱ በፊትም ሆነ በኋላ በተለያየ ጊዜ ከህገ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለው በኃጢአታቸው ምክንያት አምላካቸውን ያስቆጡ ህዝቦች እንደነበሩ እንረዳለን። ዘፍ 6፥1  ዘፍ 11፥1  1ኛ ሳሙ 2፥31



ሬ ላይ ያለውን ትውልድ ስንመለከት  በዝብርቅርቅ አመለካከት ውስጥ እየዋኘ ለዛሬም ሆነ ለነገ የሚሆን መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት አቅቶት በድንግዝግዝ  ዓለም እንደገደል ዛፍ የሚወዛወዝ አሳዛኝ ትውልድ እየሆነ ነው። ይሁን እንጅ ዓለምን ንቀው በገዳም ተወስነው ሌት ተቀን ስለዓለም የሚጸልዩትን የእግዚአብሔር ምርጦች ስናስብ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የተዘረጋ እጁ እንዳልታጠፈ እንረዳለን።   

አሁን በእኛ ህይዎት እየታየ ያለው፥  ህልም አይሉት ቅዠት፣ ራዕይ አይሉት ተስፋ በደመነፍስ የምንጓዝ ውሃ የሌለባቸው ደመናዎች እንደተባሉት ህዝቦች ፍሬ አልባ ተክሎች እየሆንን ነው።የህልምና የቅዠት ልዩነት የሚታወቀው በተግባራቸው ነው።  አንዳንድ ጊዜ ህልም የሚመስል ቅዠት አለ። ቀን ቆሎ ቆርጥሞ የሚውል የኔ ቢጤ ሌሊት ጮማ ሲቆርጥ ሊያድር ይችላል። ታዲያ ይህን ሰው ብትጠይቁት በህልሜ ጮማ ስቆርጥ አደርኩ እንጅ የሚላችሁ ቃዠሁ ሊል አይችልም። ምክንያቱም ቅዠት እንደ ስድብ ስለሚቆጠር ማለት ነው።  አንድ ነገር ይበልጥ ስድብ ሊሆን የሚችለው አለቦታው ሲገባ ነው።     

የሰው ልጅ በሥጋው ከአራት ባህርያት የተፈጠረ በመሆኑ እንደተፈጥሮውም አራት ዓይነት ባህርይ ይታይበታል። ባህርያቱም፥ እሳትነት፣ ውሃነት፣ ነፋስነት፣ አፈርነት ናቸው። ህያው ሆኖ እንዲኖር ከግዚአብሄር በተሰጠው እስትንፋስ ሶስት ባህርታት አሉት። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ከስጋዊ ዓለም ይወጣና በመንፈስ የሚጓዝበት ጊዜ አለ። ዓይነ ስጋ እንዳለው ሁሉ አይነ ህሊናም አለው። እግረ ስጋ እንዳለው ሁሉ እግረ ህሊናም ተሰጥቶታል። ስጋዊው አካል የሚታመም፣ የሚራብ፣ የሚጠማ ወይንም ደግሞ በተለያየ ምክንያት ሊጎድል የሚችል ሲሆን መንፈሳዊው አካል ግን ይህ ሁሉ የለበትም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ባለን መንፈሳዊ አካል በጎ ነገር ካላሰብንበት የመንፈስ አካለ ጎደሎነት ሊገጥመን ይችላል።
ህልም ወይንም ራዕይ በአካለ ሂሊና የሚከሰት ድርጊት ነው። ህልምና ራዕይ ተመሳሳይነት አላቸው። ሰዎች በተለያየ ጊዜ ህልምን ያልማሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው መልካም የሆነ ህልም አለ። ዘፍ 28፥12  የማይገባ ህልም በእግዚአብሔር ዘንድ ሚጠላ ህልም አለ። ዘዳ13፥1 ሰው በራሱ ህልም መተማመን አይገባውም ኤር 29፥8 በቀድሞው ዘመን እግዚአብሔር ለነገስታቱ  1ኛ ነገ 3፥5 እንዲሁም ለህዝቡ ሊያደርጉት የሚገባውን  ወይንም ደግሞ ሊያደርጉት የማይገባውን እንዲሁም ወደፊት ሊደርስባቸው የሚችለውን ነገር አስቀድሞ በህልም እየታየ ይነግራቸው ነበር።
ወደ ሃሳቤ ልግባ። ቃል ቃላትን ሲወልድ ምስጢር ስቦኝ እንጅ፥ ጥቂት ለመጻፍ የፈለኩት እኛ እንዴት ነን? ምን እያለምን ነው? ምንስ ራዕይ ታየን? ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ ለነገ የሚሆን እያተረፍን ያለነው ምንም ፍሬ ነገር አልታይህ ቢለኝ ነው። ሁላችን የምንደክምለት ነገር በፍቅር ፣ በትህትና፣ በፈራሄ እግዚአብሔር የተደገፈ ስላልሆነ ፍሬ ይገኝበታል ለማለት አያስደፍርም።

ቀድሞ የነበሩ አባቶቻችን እግዚአብሔር በህልም ወይንም በራዕይ እየተገለጸ ያነጋግራቸው ነበር ለምን ስንል አይዋሹም፣ አይሰርቁም፣ ኃጢአታቸውን አይደብቁም፣ እለት እለት በንስሃ ወደእርሱ  ይቀርባሉ ሌላ የተለየ ከሰውነት የወጣ መለዓካዊ ተፈጥሮ ኖሯቸው አልነበረም። አንዳንድ ሰዎች በኛ ላይ ስለሚሆነው ነገር ያላቸው ግምታዊ ትርጉም እግዚአብሔር ከኛጋር የሌለ አድርገው ያስባሉ። ነገር ግን እርሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋራ ነው  <<  እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ  ማቴ 28፥20 >> ዛሬ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ባይሆን ኖሮ እንደጠላቶቻችን መብዛት በእውነተኛዋ እምነት ጸንተን መኖር ባልቻልንም ነበር። አሁን በኛ በኩል ያጣነው ትህትናን ነው። እግዚአብሔር ከኔ የተሻለ ሰው አለው ማለት ነው ያቃተን።

በምድረ ኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም እግዚአብሔር የመረጣቸው እለት እለት በፊቱ የሚንበረከኩ አስቀድሞ ለዚህ ክብር የመረጣቸው ብዙ አገልጋዮች አሉት። ስለነሱ ብሎ የስሙ መጠሪያ የሆነችውን ቤተክርስቲያን እንድትጠፋ ፈቃዱ አይደለም።

ባለንበት ዘመን የቤተክርስቲያን ፈተናዎች እጅግ ብዙ ናቸው። የውጭውን ስንመክት ከውስጥ ያለው እየሸረሸረ ውስጣችንን ሰላም በመንሳት ሊያለያየን እየሞከረ ነው። እርስበርሳችን በምንፈጥረው የቃላት ጦርነት ለውጭው ጠላት መንገድ እየከፈትን ነው። መለያየታችን እኛን ሲጎዳ ጠላትን ግን በብዙ ይጠቅማል። ለዚያ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ 5፥15 << ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ >> ያለው ። ከሁላችን የሚደመጠው ሃሳብ ጠቃሚ ጠቃሚ ሆኖ ሳለ። ነገር ግን የጉዳዩ ፈጻሚ ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚነግረን ሰው ነው ያጣነው ።ወይንም ደግሞ ሲነገረን የምንሰማበት ጆሮ ነው የተነሳነው። በቤተክርስቲያን ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁላችን መልስ ለመስጠት ስንሽቀዳደም ነው የምንታየው ነገር ግን መልሳችን የሚጀምረውም የሚጨርሰውም  በሌላው ላይ በመፍረድ ነው ። ወንጌሉ ግን እንዲህ ነው የሚለው  

እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።
በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ።
አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ >> ማቴ 7፥1

ታዲያ በቃሉ እራሳችንን ስንመዝነው እራሳችንን የት አገኘነው? ዓለማችን በብዙ ነገር አንድ እየሆነች ነው እኛጋ የሚታየው አንድነት ደግሞ በአንድ ነገር ብቻ ነው ሁላችን ከሳሾች ነን ። ከኛ ወገን ያልተከሰሰ የለም ያልከሰሰም እንዲሁ ። እያንዳንዳችን የራሳችን ፋይል ተከምሮ የሰው ፋይል ነው የምናገላብጠው ። ከሳሽ የተከሳሽን መብት ቢያውቅ ኖሮ ወደ ክስ ባልሄደ ነበር  እንደሚባለው እኛ የፈረድንበት ሁሉ ወንጀለኛ ነው ማለት አይደለም። ሁላችን የአንድ አባትና እናት ልጆች ሆነን ሳለ አንዱ አንዱን ሲያሳድድ ሰዶ ማሳደድ ሆነ ስራችን። ወንጌል በምንሰብክበት ጊዜ ወጥመድ ስናጠምድ መንጋው በአውሬ እየተበላ ነው። ህግንና ሥርዓትን ለዓለም ያስተማረች ቤተክርስቲያናችን ህገወጦች እንደፈለጉ የሚንሸራሸሩባት ሆናለች። ዛሬ መናፍቃን በግልጽ በቤተክርስቲያናችን ጉያ ውስጥ ሆነው አላማቸውን እያራመዱ ነው። አቋማቸው እየታወቀ የክህደት ትምህርታቸው በግልጥ እየተሰማ ምዕመናንን በጥርጥር ማዕበል ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ፥ ነገር ግን በመርዛማ አንደበታቸው አባቶቻችንን እየሸነገሉ እኩይ ተግባራቸውን ለማስፋፋት እድሜ እየተቸራቸው ነው። 

ለዚህ መፍትሔው የቤተክርስቲያን ልጆች አንድ ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርገንን ፍቅር ተላብሰን ወደ ጥንቱ ማንነታችን መመለስ አለብን። ለዚህም ደግሞ በመነቃቀፍ ፈንታ መደጋገፍን፣ በመለያየት ፈንታ አንድ መሆንን፣ በመናናቅ ፈንታ መከባበርን፣በመለፍለፍ ፈንታ መደማመጥን፣ ገንዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል። አባቶቻችን ዛሬ ላይ በዓለም የሚያኮራ ታሪክንና ባህልን ትተውልን ያለፉት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጋቸው ነው። ዛሬ የምንፈልገውን ማድረግ ያልቻልነው ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ በማለታችን ነው። ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ም 15 ቁ 4 እስከ 17 የተናገረውን እንመልከትና ይብቃኝ።

በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።
በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።
ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ።
እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።
ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ።
እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።
እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።
ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።
እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።
እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ።

No comments:

Post a Comment