በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ድርጊትን የሚያመለክቱ የተለያዩ የመገለጫ ቋንቋዎችን ወይንም ደግሞ ስሞችን እናገኛለን በእኛ ሀገርም ድርጊታዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ስሞችን እንጠቀማለን ከነዚህም አንዱ << የእንጀራ ልጅ >> የሚለው ነው።
የእንጀራ ልጅ ከስሙም እንደምንረዳው እውነተኛ ልጅ ያልሆነ እና እናት የተባለችውም የልጆች አባት የሆነ ባል ስላገባች እንዲሁም እንደወለደቻቸው ልጆቿ አድርጋ እንጀራ ስላበላች እንጅ ስለወለደች አይደለም ። የእንጀራ ልጅ ሁልጊዜ ለእንጀራ እናቱ የሚሰጣት ፍቅር በምታበላው እንጀራ ይወሰናል። እስኪጠግብ የበላ እለት እናቴ ይላታል አንድ ቀን የጎደለበት ጊዜ ግን ስሟን ማጥፋት ይጀምራል። ምክንያቱም ያገናኛቸው እንጀራ እንጅ በስጋ 9 ወር ከ 5 ቀን በማህጸኗ ተሸክማ አልወለደችውም። ከስጋዋ ስጋን ከነፍሷ ነፍስን የወሰደ ቢሆን ግን አካሉ ነችና ህመሟ ያመዋል፣ ደስታዋ ያስደስተዋል፣ ስሟ በክፉ ሲነሳ አይወድም፣ ከራሱ በላይ አብልጦ ይወዳታል። የእንጀራ ልጅ ግን ከሷ የተሻለ የምታበላው የምትንከባከበው ካገኘ ያችንም እናቴ ነሽ ይላታል። ነገር ግን አሁንም ጥቅሙ ከቀረበት ሌላ ፍለጋ መሄዱ አይቀርም ምክንያቱም መሰረታዊ ግንኙነታቸው ጥቅም ስለሆነ ማለት ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር በአንድ ወቅት የተናገሩትን አስታውሳለሁ << አንድ ሰው ለጥቅም ብሎ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ከሆነ የተሻለ ጥቅም ካገኘ ሰይጣንንም ከማገልገል ወደኋላ አይልም ብለው ነበር >> ስጋዊ ጥቅም ከእግዚአብሔር መንግስት ይለያል። ሰው ደግሞ ከእግዚአብሔር መንግስት ከተለየ ሰው መባሉ ከንቱ ነው። በተለይ እንኳን የእግዚአብሔርን ቤት ለማገልገል የተመረጠ ይቅርና በክርስቶስ ክርስቲያን ተብሎ በስሙ የከበረ ሁሉ በስጋዊ ጥቅም መታለል አይገባውም። ይህን ስል በህይዎታችን የምናውቃቸው ብዙ መልካም ሰዎች ይኖራሉ ። የእናትን ውለታ ስለተረዱ ሴት ለተባለች ሁሉ ክብር የሚሰጡ፣ የእንጀራ እናታቸውን ከወለደቻቸው ልጆቿ አብልጠው የሚንከባከቡ እንዳሉ ባለመዘንጋት ነው። ብዙ ጊዜ ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን ስንመለከት በመብል ምክንያት ከክብራቸው ሲዋረዱ እናያለን። በኦሪት ዘፍ ም 25 ተጽፎ የሚገኘውን ታሪክ ስንመለከት በዘመኑ ትልቅ ክብር ሆኖ የሚሰጠውን ብኩርና በእንጀራና በምስር ወጥ የለወጠ ሰውን እናጘኛለን። << ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት ዘፍ 25፥34 >> ይህ ሰው በወቅቱ የሆዱ ፍላጎት እንጅ የታየው አሳልፎ የሚሰጠውን ክብር ዳግመኛ ሊያገኘው እንደማይችል የሚያስብበት ህሊና አልነበረውም። ቢያስበውም እንኳን ሆዱን የሚወድ በመሆኑ ብኩርና ለሱ ምንም ማለት አልነበረም። ነገር ግን በፈለጋት ጊዜ ምን ብዙ ቢደክም ዳግመኛ ሊያገኛት አልቻለም።
ሌላው ችግር እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በምድር ስለሚበሉትና ስለሚጠጡት እንጅ ስለሰማያዊ ክብር አለመጨነቃቸው ነው ። የወንጌሉ ቃል ግን እንዲህ ይላል << ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ሉቃ 4፥4 >> ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስጋዌው ብዙ ህዝብ ይከተለው እንደነበረ ተጽፏል ነገር ግን እርሱ ሁሉን አዋቂ በመሆኑ ማን ለምን ይከተለው እንደነበር ተናግሯል << ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ዮሐ 6፥26 >>እናትና እምነት አንድ ጊዜ ነው የሚሰጡት የሚገኙትም ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ በጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል። አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ጸጋ አክብረን ብንይዝ ክብራችን ዘለዓለማዊ ይሆናል። ለዚያ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልእክቱ << እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና ዕብ 3፥34 >> ያለው። እናት ማለት ደግም በጎም ትሁን ክፉ ለልጇ መልካም ነች። እሷ እየተራበች ልጇን ትመግባለች ። እስከ ሞት ድረስም ቢሆን ስለ ልጇ የማትሆነው ነገር የለም። ለዚያም ነው በቅዱሱ መጽሐፍ << እናትህን ባረጀች ጊዜ አትናቃት ምሳ 23፥22 >> ከትዕዛዛት አንዱ << አባትህንና እናትህን አክብር እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር እድሜህ እንዲረዝም ዘጸ 20፥12 >> ነው የሚለው።
የእናትን ውለታ መዘንጋት እድሜን ያሳጥራል ። አንድ ፍጡር ወደዚህ ወደማያውቀው ዓለም ሲመጣ ተንከባክባ በደስታ የምትቀበል እናት ነች ። በልጇ ብዙ ችግርና ፈተና ይደርስባታል። ነገር ግን ለምን ልጅ አገኘሁ ብላ አትመረርም። ታዲያ ይህ ውለታ እንዴት ይዘነጋል?
እናታችን ማነች? እናታችን አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታችን ነች። ይሁዳ 1፥3
እናታችን ከመስቀሉ ስር ያገኘናት እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ነች ሉቃ 19፥26
እናታችን ጌታ በደሙ የዋጃት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት ማቴ 16፥18 የሐዋ ሥ 20፥28ዛሬ በቤተክርስቲያናችን የእናታቸውን ውለታ የዘነጉ፣ ልጆች ሳይሆኑ ልጆችሽ ነን እያሉ የሚያታልሉ የእንጀራ ልጆች በውስጧ ተሰግስገዋል። እንኳን የዘለዓለም ክብር የምታሰጠን እናታችንን ይቅርና ወር በስጋ የወለደችን እናታችንን ባናከብር ፍርድ ከእግዚአብሔር ይጠብቀናል። << እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። ዘጸ 21፥15 እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል። ዘጸ 21፥15 እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን ዘዳ 27፥16 እናቱን የሚሰድብ፥ በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል።ምሳ 20፥20 >> ለትልቁ ማዕረግ የደረሱ እውነተኛ የተባሉ ልጆቿም በጊዜያዊ ጥቅም እየተደለሉ ድምጿን ከመስማት ወዷኋላ ብለዋል። ገንዘብ ፣ ስልጣን ፣ ውዳሴ ከንቱ ፣ አሸንፏቸው እያዩ ፣ እየሰሙ ዝምታን መርጠዋል ። ይህች እናት ዛሬ አቤት ፣ወዴት እሚላት ትፈልጋለች። እስቲ ማነው ዛሬ ከቂም ፣ከበቀል፣ ከዘረኝነት፣ ከራስ ወዳድነት እርቆ አለሁሽ እናቴ የሚላት? የብዙ ቅዱሳን እናት የብዙሊቃውንት መፍለቂያ የሆነች እናት ልጅ አልባ መባል የለባትም። ያለንበት ዘመን ወዮ ለዚህ ትውልድ ቤተክርስቲያን እንባዋ ጎርፍ ሆኖ እንዳያሰጥመው ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ንስሃ እንዲገባ ማን በነገረው የሚያሰኝ ነው።
ጥበበኛው ሶሎሞን በምሳሌው << ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው ምሳ 6፥20 >> እንዳለው ዛሬ በብዙዎቻችን ላይ ችግርና ፈተና የመጣው ህገ እግዚአብሔር በመናቁ፣ የቤተክርስቲያን ድምፅ ባለመሰማቱ ነው። ቤተክርስቲያን ምሉዕ በኩለሄ ስለሆነች አንዳች ነገር አይጨመርባትም ያላትን ክብርና ጸጋ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል እንጅ ህግና ስርዓቷን መሸራረፍ አይገባም << አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ ምሳ 22፥28 >> አንዳንድ ጊዜ ሰላም የለንም፣ ሰላም አጣን ስንል እንሰማለን። ለሰላም ማጣታችን ትልቁ ምክንያት አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ህግና ስርዓት ጥሰን በራሳችን እንጓዛለን ማለታችን ነው << አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር በምትወርሳት ርስትህ የቀደሙ ሰዎች የተከሉትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንቀል። ዘዳ 19፥14 >> ይላል ። ይህን ብናደርግ የሚደርስብን ነገር ተጽፏል << በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል። ምሳ 30፥17 >> ማስተዋል ባለመቻላችን በበደል ላይ በደል እንጨምራለን። ትልቁ ህግ ፍቅር ተሽሮ ሰላም ማግኘት አይቻልም ። ከሁሉ በፊት ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረቢጽ ( እግዚአብህርንና ባልንጀራን መውደድ) ተሽሮ እንዴት ነው ሰላም የሚታሰበው? << ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ገላ 5፥14 ሰው እግዚአብሔርንና ባልንጀራውን ከወደደ ከሰይጣን ወጥመድ ማምለጥ ይችላል። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ከሌሉት ግን ሁልጊዜም በሰይጣን እንደተፈተነ፣ እንደተሸነፈ፣ እንደተቅበዘበዘ ነው የሚኖረው። ዘፍ 4፥14 በተለይም ደግሞ ለባልንጀራው ክፉ የሚመኝ ከሆነ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋራ የለም። የወንድሙን ደም እንዲያፈስ ሰይጣን ልቡን እንዳነሳሳው እንደ ቃየን መንገዱ ሁሉ ክፉ ነው የሚሆነው። መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት << ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ መዝ 50፥20 >> ነው ያለው። ዛሬ ወንድም ለወንድሙ አንዱ ለሌላው ወጥመድ ሲያጠምድ ነው የሚታየው። የሰው ውድቀት የሚያስደስታቸው ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ያከበረውን የሚያዋርዱ አሉ። << ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ ሮሜ 13፥7 ይላል ቃሉ ታዲያ የእግዚአብሔርን ቃል እኛ ካላከበርነው ማነው የሚያከብርልን? ማነውስ እኛን የሚያከብረን? በሽበታሙ ፊት ተነሳ፥ ሽማግሌውንም አክብር አምላክህንም ፍራ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ዘሌ 19፥32 እንግዲህ ይህን ያህል መናገር ከቻልን ዋናው የጽሁፉ ዓላማ ሁላችንም የኔ ድርሻ ምንድነው? እናቴ ከኔ የምትጠብቀው ምንድነው? የጎደለኝ ነገር ምን አለ ብለን እራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል እንድንመዝን ነው። ምናልባት አንዳንድ ሰዎች እንደሚተረጉሙት አንዱን ጻድቅ አንዱን ኃጥዕ ለማለት አይደለም። ኃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው በ2ኛው መልዕክቱ << በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታ ቃል እንዲሮጥ በእናንተም ዘንድ ደግሞ እንደሚሆን እንዲከበር፥ እምነትም ለሁሉ ስለማይሆን ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ስለ እኛ ጸልዩ 2ኛ ተሰ 2፥1 >> እንዳለው ስለ አገልጋዮች ጸልዩ እንጅ በማንም አትፍረዱ ። ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋራ ይሁን |
No comments:
Post a Comment