« መድኃኒታችን እነሆ ተወለደ »
የሰው ልጅ ለአምስት ሽ አምስት መቶ ዘመን በኃጢአት ደዌ በጸና ታሞ የሚፈውሰው መድኃኒት በማጣቱ በጨካኙ በዲያቢሎስ አገዛዝ ስር ወድቆ የፍዳና የኩነኔ ዓመታትን አሳልፏል። ተቆራኝቶት የነበረው ሰው ሊፈውሰው የማይችለው ደዌ ስለነበረ በየዘመኑ የተነሱ ጠቢባን ብዙ ቢደክሙም መድኃኒት ማግኘት ግን አልቻሉም ነበር።
ቢሆንም ግን የተያዘበት በሽታ ባለመድኃኒቱ እስኪገለጥ ድረስ ቢያሰቃየውም ፈጽሞ እንዲያጠፋው የፈጣሪው ፈቃድ አልነበረምና ያንን መድኃኒት በየዘመኑ የነበሩት አበው ተስፋ ባለመቁረጥ ሲጠብቁ ኖረዋል። « እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ። ዘፍ 49፥18
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ « እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። መዝ 74፥12 ብሎ እንደተናገረው የመከራው ዘመን ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ አንድኛ ልጁን ለዓለም መድኃኒት ይሆን ዘንድ ልኮታል።
ብዙ ነቢያት የተነበዩለት፣ ብዙ ጻድቃን ተስፋ ያደርጉት የነበረው መድኃኒት በቤተልሄም አውራጃ በከብቶች በረት ተወለደ። ለብዙዎች ቤዛ ሊሆን ወደዚህ ዓለም የመጣው ጌታ እንደ ምስኪን በግርግም በጨርቅ ተጠቅልሎ መገኘቱ ብዙዎችን አስገረመ። ነገር ግን አስቀድሞ በትንቢት « ናሁ ሰማእናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ኦመ ገዳም ንበውዕ እንከሰ ወስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር ወንሰግድ ውስተ መካን ኃበ ቆመ እግረ እግዚእነ » ( እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን።መዝ 132፥6) ተብሎ ተነግሮ ነበር ያ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በቤተልሄም ግርግም የዓለሙ ሁሉ ጌታ መድኃኔዓለም ተወለደ። እንዲሁም ነቢዩ ሚክያስ « አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።» ሚክ 5፥2 ብሎ ተናግሮ ነበር።
እንደተናገረውም ታናሿ የኤፍራታ ምድር ቤተልሄም ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆን ቦታ ስላልነበራት በከብቶች በረት የዓለሙን ጌታ አስተናግዳለች። በዚህም የተነሳ የዓለም ሃያላን መንግስታት ትኩረታቸውን ወደሷ አድርገዋል። ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል « ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።እርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።» ማቴ 2፥1
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለእኛ ለክርስቲያኖች ታላቅ ደስታን አጎናጽፎናል። ለብዙ ሽ ዓመታት ሰውና መላእክት የተፈጠሩት ለአንድ አላማ ሆኖ ሳለ አዳም በበደሉ ምክንያት የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር በህብረት እግዚአብሔርን የማመስገን ጸጋውን ተነስቶ ነበር። በጌታ መወለድ ግን ሰውና መላእክት እግዚአብሔርን በህብረት አመስግነዋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው « በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ።ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።» ሉቃ 2፥1
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በስጋ ማርያም መገለጥ ስናስብ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር እንረዳበታለን። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ « ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 1ኛ ዮሐ 4፥7 » ብሎ ተናግሯል።
እግዚአብሔር አምላክ ከራሱጋር መክሮ ማንም ሳያስገድደው ስለሰው ፍቅር ሲል አንድ ልጁን በድንግል ማርያም ማህፀን እንዲያድር አደረገው፣ በድንግልም ማህጸን ተጸነሰ፣ የሰውንም ሥጋ ለበሰ፣ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው መወለዱም በመንፈስ ቅዱስ ታወቀ፣ ህሙማንን ፈወሰ፣ የተፍገመገሙትንም አጸና፣ በሲኦል የተጣለውን አዳምንና ልጆቹን ፈልጎ አገኘ፣ ከሞት ባርነትም ነጻ አወጣው፣ ሞትንም ሻረ፣ የሰይጣንንም የተንኮል ማሰሪያ ቆረጠ ሲኦልንም ዘግቶ የህይዎትን በር ከፈተልን፣ በጨለማ ይኖሩ የነበሩ ብርሃን አገኙ፣ ጨለማንም አራቀ፣ ወደዘለዓለም ህይዎት የምንገባባትን ስርዓትም ሰራልን።
ዛሬ ለሁላችን የሚያስፈልገንን ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት፣ መከባበር፣ መተዛዘን፣ ልናገኝ የምንችለው ስለኛ ፍቅር ሲል ከክብሩ ዝቅ ብሎ እንደምስኪን ድሃ በቤተልሄም በከብቶች በረት የተወለደውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ስንችል ነው። አለበለዚያ ግን በዓል አክባሪዎች ብቻ ሆነናል ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ « እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።» 1ኛ ቆሮ 11፥1» ብሎ እንደተናገረው የጌታን ልደት ስናስብ ትህትናውን፣ ፍቅሩን፣ ርኅራሄውን፣ ቸርነቱን፣ እያሰብን መሆን አለበት። ከዚሁም ጋር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የራቁትን በማቅረብ የደከሙትን በመደገፍ፣ ምክርና ተግሳጽ የሚያስፈልጋቸውን በፍቅር መምከርና መገሰጽ ከኛ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ነው። በዚህ መንገድ ተጉዘን ኃጢአታችንን በንስሃ አጽድተን፣ ቅዱስ ስጋውን በልተን፣ ክቡር ደሙን ጠጥተን፣ ኑ ያባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግስተ ሰማያትን ውረሱ ከሚላቸው ከቅዱሳኑ እንዲደምረን የአምላካችን ቸርነቱ፣ የወላዲተአምላክ ምልጃና ጸሎት፣ የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት፣ የቅዱሳን መላእክት ጥበቃና ተራዳኢነት ከሁላችን ጋራ ይሁን።
No comments:
Post a Comment