Saturday, January 21, 2012

ከእኔም ተማሩ

በቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ምክንያት በማድረግ በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በዓይነቱ ልዩ የሆነ በዓልም እናደርጋለን። ይህ ለምን ሆነ ብንል፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የፈጸማቸው ነገሮች በሙሉ በቤተክርስቲያናችን ትርጉም ስላላቸው ነው። ሌሎችአብያተ ክርስቲያናት የጌታን በዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ መጠመቅ ከመናገር ያለፈ ትርጉም አይሰጡትም።


በቅዱስ ወንጌሉ እንደተጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደጋግ ተአምራት ያደረገባቸውን ምኩራባት ኮራዚ፣ ቤተሳይዳ፣ ቅፍርናሆምን ባዩት በሰሙት ነገር ባለመማራቸው እና ንስሃ ባለመግባታቸው ነቅፏቿዋል።

እነሱ በአይናቸው አይተው ያላመኑበትን ሌሎች አህዛብ ዝናውን ሰምተው እንደሚያምኑበት ያውቅ ነበርና ከሰዶምና ከገሞራ ያነሱ መሆናቸውን በምሳሌ ሲናገር ።  ወንጌላዊዉ ማቴዎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል፦

በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ፦

ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራትበጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና።

ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።

አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና።

ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። ማቴ 11፥20

ጌታ ይህን የተናገረው በቃሉ አስተምሮ በእጁ ተአምራት አድርጎ ነገር ግን ያንን አይተውና ሰምተው መለወጥ ላሉቻሉት ህዝቦች ነው። ከዚህ የምንማረው ዛሬ በምንሰማውና በምናየው ነገር መማርና መለወጥ ካልቻልን፣ ንስሃ ባለመግባታችን ከእግዚአብሔር ወቀሳ የማንድን መሆኑን ነው።

ከጥምቀቱ ምን እንማራለን ?

የሰማይና የምድሩ ንጉስ፣ ሁሉን በእጁ የያዘ፣ ከሆነው ሁሉ ያለእርሱ ፈቃድ አንዳች ነገር የሆነ የሌለ ሲሆን ነገር ግን ትህትናን ለማስተማር ነውና በሥጋ የተገለጠው በፍጡሩ  እጅ ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደ። አስቀድሞ በንስሃ መንገዱን እንዲጠርግ የተላከው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በማቴ 3፥11 እኔ ለጠጅ ብርሌን ለልብስ ገላን እንዲያጥቡለት ለሱ ጥምቀት የሚያበቃ  ጥምቀት አጠምቃችኋለሁ ለሱ ተአምኖ ኃጣውእ በሚያበቃ ተአምኖ ኃጣውእ አስተምራችኋለሁ እንጅ ክርስቶስ አይደለሁም። ከኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከኔ አስቀድሞ የነበረው ነው። እሱ የባሕርይ አምላክ ነው። እኔ ግን የእግሩን ጫማ ልፈታ የማይገባኝ ነኝ ። እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ እሱ ግን በእሳት ያጠምቃችኋል እያለ ያስተምር ነበር።

በዚያን ጊዜ ነው ጌታ ትንቢቱን ሊፈጽም፣ ትህትናን ሊያስተምር፣ የእዳ ደብዳቤያችንን ሊደመስስ ከገሊላ ተጉዞ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ የወረደው። ምነው ባሪያ ወደጌታው፣ ወታደር ወደንጉስ ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደ ባሪያ፣ ንጉስ ወደ ወታደር እንዴት ይሄዳል ቢሉ ስለ ትህትና ነው። ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው ስለ  ትህትና ነው እንጅ ስለ ልዕልና አይደለም።

እንዲሁም አብነት ለመሆን ነው። ጌታ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ዛሬ ነገስታት መኳንንት መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር። ወደ ቤተክርስቲያን ወደ ካህናት ሄዶ መጠመቅ እንደሚገባ ሲያስረዳ ነው። በዮርዳኖስ መጠመቁ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው።   መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 114፥4 ላይ  

ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ።

አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል?

እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?

ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት ምድር ተናወጠች ብሎ እንደተናገረው። ያንን ትንቢት ይፈጽም ዘንድ ነው።

 እንዲሁም ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች ወርዶ ይገናኛል። ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ እንደሆነ የሰው ሁሉ ነቁ (መገኛው ) አንድ አዳም ነው ። ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አህዛብ በቁልፈት ተለያይተዋል። ከታች ወርዶ በወደብ እንዲገናኝ  ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ በጥምቀት አንድ ሆነዋል። እንዲሁም ሌሎች ብዙ ምሳሌዎች አሉት   ድውያን ተፈውሰውበታል 2ኛ ነገ 5፥14 ልዩ ልዩ ተአምራት ተደርጎበታል   ኢያሱ  3፥13  2ኛ ነገ 2፥14

ዛሬ ላይ ሆነን በዓለ ጥምቀቱን ስናስብ እራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና ወደ ዮርዳኖስ የወረደውን ጌታ እያሰብን እራሳችንን ከፍ ከማድረግ ዝቅ ወደማድረግ ፣ በራሳችን ከመመካት በእግዚአብሔር ወደመመካት፣ ከትዕቢት ወደ ትህትና፣ ከክፋት ወደ ደግነት፣ ከቂም ከበቀል ወደ ይቅርባይነት፣ ከመነቃቀፍ ወደ መደጋገፍ፣ ከሃሜት ወደ ጸሎት፣ ከድፍረት ወደ እግዚአብሔርን መፍራት መለወጥ አለብን።

ጌታ የተጠመቀው እራሱ እከብር ብሎ አይደለም እሱማ አክብሩኝ አይል ክቡር፣ አንግሱኝ አይል ዘለዓለማዊ ንጉስ፣ አበድሩኝ አይል ባለጸጋ ነው እኛን ሊያከብረን ነው እንጅ። እራሱ እነጻ ብሎ አይደለም እኛን ከኃጢአት ከበደል ሊያነጻን ነው ነው እንጅ። ስለዚህ ጌታ እራሱ  በማቴ 11፥29 እንደተናገረው ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ  እንዳለው በህጉና በትእዛዙ ተጉዘን እረፍት በሚገኝባት በመንግስተ ሰማያት ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንድንኖር በቸርነቱ ይርዳን። 

የበዓሉ በረከት በሁላችን ላይ ይደር አሜን

















No comments:

Post a Comment