Sunday, January 1, 2012

መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ት,ዘካ 11፥17

ዛሬ እለቱ ታህሳስ 22/ 2004 ዓ/ም ሲሆን  እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህ እለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የመጽነሷን ዜና የነገረበት እለት ነው። ከዚሁም ጋር እለቱ እለተሰንበት ላይ ስለዋለ ድርብ በዓል ነው። ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዛሬውን ሰንበት ኖላዊ ወይንም ደግሞ መልካም እረኛ የሚል ስም ሰጥቶታል። ያለፉት ሁለት ሳምንታት እና የዛሬው ሰንበት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከድንግል ማርኃም በስጋ መወለድ እያሰብን የልደቱን ብርሃን ለማየት በተስፋ ደጅ የምንጠናበት ነው።


ወደ ቅዱስ ያሬድ የእለቱ ስያሜ ስንመጣ  መልካም እረኛ የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ፍቅር ሲል ወደዚህ ዓለም መጥቶ በዲያቢሎስ ቁራኝነት ተይዞ ሲንገላታ የነበረውን አዳምን ከወደቀበት እንዳነሳው እያሰብን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር  ምን ያህል እንደሆነ የምንረዳበት ነው።

ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። ማቴ 9፥34   እረኛ የሌለው መንጋ አውሬ በመጣ ጊዜ ይበተናል። ከአውሬ ያመለጠው በዱር በገደል ሲባዝን መጨረሻው ጥፋት ነው። ስለዚህ መንጋ ሊኖር የሚችለው እረኛ ሲኖር ነው። አዳም የፈጣሪውን ህግ በማፍረሱ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ፣ በማጣቱ እረኛ እንደሌለው መንጋ ወደ ምድረ ፋይድ ተጥሎ ከነልጆቹ በዲያቢሎስ ባርነት ስር በመውደቁ ምክንያት እግዚአብሔር አዘነለት። ጥንትም በዲያቢሎስ የተንኮል መረብ ተጠልፎ እንደወደቀ ያውቅ ነበርና በማይመረመር ጥልቅ ፍቅር ሊያድነው ወደደ። እናም በህይዎት ያሉ 99ኙን  መንጋዎች ትቶ በክፉ አውሬ እየታደነ ያለውን አንዱን በግ አዳምን ፍለጋ ከክብሩ ዝቅ ብሎ ወደዚህ ዓለም መጣ    

ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ም 10፥1 ላይ       « እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።» እንዳለው   እውነተኛ እረኛ ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው ክርስቶስ ስለ መንጋዎቹ ለሞት ተላልፎ እስከመሰጠት ደርሶ አዳምንና ልጆቹን ከክፉ አውሬ ከዲያቢሎስ ነጥቆ ነጻነትን አጎናጽፏቸዋል።

ጌታችን ለቅዱስ ጴጥሮስ ትወደኛለህን?ብሎ በጠየቀው ጊዜ አዎን ጌታ ሆይ እንድዎድህ አንተ ታውቃለህ ብሎ መልሷል። ልብንና ኩላሊትን መርምሮ የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ ያውቅ ነበርና እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለ። የእምነቱን ጽናት አይቶ  በጎቼን ጠብቅ አለው።

ቀደም ሲል የነበሩት የቤተክርስቲያናችን አባቶች ማንኛውንም ሰው ለክህነት በሚመርጡበት ጊዜ የተለያዩ የእምነት ጽናት መለኪያዎችን ያደርጉ ነበር ። ምክንያቱም ኃላፊነቱ ከባድ ስለሆነ ስለመንጋው የሚጨነቅ መሆኑ እንዲሁም ለመንጋው የሚራራ እና የተመሰከረለት ነበር ለእረኝነት የሚመረጠው። ከላይ በወንጌሉ እንደተገለጸው መንጋዎቹ የሚያውቁት፣ እሱም የሚያውቃቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው፣ እሱ ከፊት ሲሄድ ከኌላ የሚከተሉት ነበር የሚመረጠው። ያ ዘመን መልካም ነበር ብለን ለመናገር የምንደፍርበት ብዙ ምክንያት አለን። ዛሬ ላይ የእግዚአብሔር መንጋዎች ምእመናን በእረኞቻቸው የሚንገላቱበት፣ መንጋዎቹም የእረኛቸውን ድምጽ የማይሰሙበት አጋጣሚዎችን አይተናል። 

እውነተኛው እረኛ  በጎቹን ወደ ዘለዓለም ህይዎት መርቶ ያደርሳል የዚህ ዓለም እረኛ ግን ለጊዜው ከአውሬና ከሌባ መጠበቅ ቢችልም
በመጨረሻ አርዶ መብላቱ አይቀርም   «   እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ዮሐ 10፥12 »  በዘመናችን እያየን ያለነው ይህን ዓይነት እረኞችን  ነው። በኋለኛው ዘመን ለመንጋው የማይራሩ ይመጣሉ ተብሎ እንደተነገረው በአደራ የተቀበልናቸውን የእግዚአብሔር መንጋዎች በአግባቡ ማሰማራት ካልቻልን የእረኞች ጌታ በተገለጸ ጊዜ ወዮልን። ከማይራሩት ከጨካኞች እንዳይመድበን ዛሬ ኃላፊነታችንን እንወጣ። 

ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ 5፥10 ላይ « በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። » እንዳለው ወደ እኛ ህይዎት ስንመለስ ሐዋርያው እንደተናገረው እንደገና ወደ አለመታዘዝ፣ ወደ ኃጢአት ባርነት መመለስ አይገባም።

ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ማቴ 23፥3  እንደተባለው  እውነተኛውን እረኛ  መድኃኔዓለም ክርስቶስን እያሰብን የማንንም ኃጢአትና በደል ሳንቆጥር ለህገ እግዚአብሔር በመታዘዝ ልጅነታችንን ጠብቀን ልንኖር ይገባናል።

No comments:

Post a Comment