Tuesday, August 16, 2011

እንደ ተቀማም አልቆጠረውም

ሰዎች አንድን ነገር ብንሰርቅ ወይም በጉልበት መንትፈን ብንወስድ ሌሎች እንዳይወስዱብን እንደብቀዋለን፤ አሊያም በጥንቃቄ እንይዘዋለን፡፡ ወደ ሥልጣን ከወጣን በኋላም መልሰን ወደ ታች መውረድ እንፈራለን፡፡ ብንወርድ እንኳን ታጅበን እንሄዳለን፡፡ ጉዞአችንም ሁሉ በፍርሃት የተመላ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የተቀመጥንበት ወንበር ከመጀመርያውኑ የእኛ ሳይሆን ሌሎች ነበሩበትና፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባርያዎቹን መልክ ይዞ ከልዕልና ወደ ትሕትና ወረደ፡፡ ሲመጣም ብቻውን መጣ እንጂ በመላእክት ወይም በሌላ ጭፍራ አልተጠበቀም፡፡ ሰው ሆኖ ራሱን ባዶ ስላደረገም ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አላስቀረበትም፤ እንደ ተቀማም አልቆጠረውም፡፡ ማንም አይወስድበትና “የባርያዎቼን መልክ አልይዝም” ብሎም አልተከራከረም፡፡ የማዳን ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ዓለም ሳይፈጠር ከአባቱ ጋር በነበረው ክብር የሚቀመጥ አምላክ ነውና፡፡ ይህ ሥልጣኑ ድሮውንም የባሕርዩ ነውና ራሱን ዝቅ ዝቅ አደረገ፤ ለሞት ይኸውም ለመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘ ሆነ፡፡

ሞታችንን ለሞተልን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁንለት፤ አሜን፡፡

Sunday, August 7, 2011

የሃይማኖት ጉዞ

       የሃይማኖትን ጉዞ በማስፈረራራት ማስቆም አይቻልም !!!ዘመኑ ሃሰት የነገሠበት ዲያቢሎስ የሰለጠነበት ሁኗል :: እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊሳደዱ ሊገፉ አግልግሎታቸው ሊደናቀፍ የሌለባቸው ክፉ ስም ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል፤ ይህን ደግሞ ጌታችን “ ስለ ስሜ በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ “ ማቴ ፳፬፥፱
በማለት እንደተናገረ በጎ እያደረግን ስለስሙ ስንነቀፍ ስንሳደድ ስንጠላ ደስ ሊለን ይገባል :: የተጠራነው ለዚህ ስለሆነ ጥርጥር በሌለበት ሃይማኖት ልንጸናም ያስፈልጋል ::

ቅዱስ ያዕቆብ “ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደሙሉ ደስታ ቁጠሩት :: ” ያዕ ፩፥፪ እንዳለ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንፈተን ዋጋ ያለው መሆኑን እንወቅ ::ፈተና ፦በእውነት እግዚአብሔርን እያገለገልን ከመጣ የምንደሰትበት እንጅ የምናዝንበት አለመሆኑን የእውነት ተጻራሪ ለሆኑ ሁሉ ማሳየት ተገቢ ነው :: ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብንነቀፍ ከኛ ጋር ያለው እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ነውና አንሸበርም :: እግዚአብሔርን ሊያሸንፍ የሚችል ማንም የለምና :: “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ::” ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲ ሥራውንም ማስተጓጎል አይቻልም ደግሜ እላለሁ ፡ በእውነት የሃይማኖትን ጉዞ በማስፈረራራት ማስቆም አይቻልም !!!

Friday, August 5, 2011

የሚያዝኑ ብጹዓን ናቸው


                          ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4
ዕንባ የተጀመረው በአዳምና በሔዋን ነው፡፡ ያለቀሱትም አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በልተው እግዚአብሔርን በመበደላቸው ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ የተጀመረው በንስሐ ነው፡፡ በቀሌምንጦስ «አልቦቱ ካልዕ ሕሊና ለአዳም ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ፤ ለአዳም ስለ ኃጢአቱ ከማልቀስ /ኃጢአቱን እያሰበ ከማልቀስ/ በቀር ሌላ አሳብ /ግዳጅ/ አልነበረውም» ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ የዕንባ ቀዳሚ ጠቀሜታ ሰውን በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ተመዝግቧል፡፡ «ወበአንብዕየ አርሐስኩ ምስካብዬ፤ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ» የሚለው ቅዱስ ዳዊት የንስሐ ዕንባውን፣ የጸሎት ዕንባውን ነው፡፡ /መዝ 6÷6/ ጌታችንም በወንጌል «ብፁዓን እለ ይላህው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌስሑ፤ ዛሬ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ የተመሰገኑ ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና» /ማቴ 5÷4/ ሲል ያስተማረው የሚገባው ለቅሶ ወይም ዕንባና ሐዘን የንስሐ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በሌላም ቦታ «እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፣ ታዘናላችሁና፣ ታለቅሱማላችሁ» /ሉቃ 6÷25/ ሲል ያስጠነቀቀን ጠቃሚውን ዕንባና ሐዘን ለማስተማር ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም «ከሳቅ ሐዘን ይሻላል፣ ከፊት ኀዘን የተነሣ ደስ ይሰኛልና፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት [በንስሐ] ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት [ኃጢአት በሚፈጸምበት ቦታ] ነው» በማለት የንስሐ ዕንባን መፈለግ ጠቢብነት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ከዚህም በላይ በቅድስና ሕይወት የሚኖሩ ቅዱሳን በዐሥሩ መዓርጋት ሲሸጋገሩ አራተኛው መዓርግ አንብዕ ይባላል፡፡ ይህም ፊታቸው ሳይከፋውና ሰውነታቸው ሳይሰቀቅ ዕንባን ከዓይናቸው ማፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ ዕንባ ይህን የመሰለ ጠቀሜታ ያለው በመንፈሳዊነትም የብቃት ደረጃ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡