Wednesday, February 15, 2023

ካህኑን ለምን???

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የክህነት አርማ የለበሰና በእጁ የክርስቶስን መስቀል የያዘ ካህን በአንድ የጥበቃ ሰራተኛ በጥፊ ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቆ በዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሲመለከቱት ሰንብተዋል ብዙዎችም በማዘን ቁጣቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል። በሌላው ዓለም ላሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ለመረዳት ሳይጠቅም አይቀርም። እኔ በግሌ በጥፊ የተማታውን ወንድም ባገኘው ለዚህ ደረጃ ያደረሰውን ምክንያት ከመጠየቅ ያለፈ ካህን ወይም ኢትዮጵያዊ በመሆኔ በእርሱ ላይ የበቀል ምላሽ ለመስጠት አልሞክርም ነገር ግን እውነቱን ለማወቅ የምጠይቀው ብዙ ጥያቄ ነበረኝ።

ካህን ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፤ የምዕመናን አባት ፤ ጠባቂ ፤ መጋቢ ማለት ነው ። ስለሆነም ስለ እግዚአብሔርና ስለህዝቡ ሲባል እንኳን አካሉ የለበሰው ልብስ ክብር ይሰጠዋል በሀገራችን በኢትዮጵያ የእምነት አባቶች ሲከበሩ ኖረዋል ስለምን ቢባል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ''እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና።ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። እብ11፥1'' እንዳለው የእምነት ሰዎች ከምድራዊው ዓለም አልፈው ስለሰማያዊው ዓለም የሚያስተምሩ በመሆናቸው ክብር ይሰጣቸዋል። ይህን በማድረግ ደግሞ ሃገራችን ኢትዮጵያ ቀዳውን ስፍራ ትይዛለች ታዲያ ዛሬ ያ አባቶችን ማክበር እምነትን ማክበር የት ሄደ? ብዞዎች እያሉት እንዳለው የካህኑ መመታት የቤተክርስቲያንን ክብር ለማዋረድና ለማንቋሸሽ የተደረገ ነው። እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ከመጥላት የተነሳ እንደሆ በግልጽ ማየት ይቻላል። ግብረገብነትንና ሰብአዊ ክብርን ስታተምር የኖረች ቤተክርስቲያን በዚህ ደረጃ እንዴት ልትጠላ ቻለች? 

Saturday, February 11, 2023

የትላንቱ እንቅፋት

ዛሬ ላይ እየመታን ያለው እንቅፋት ትላንት ከትላንት ወዲያ ሲያደናቅፈን ነበር በየወቅቱ አልፈናቸው የመጣናቸው እንቅፋቶች ቋጥኝ እየሆኑ ከእግራችን አልፈው ወደ ጉልበታችን ሊደርሱ ችለዋል::

እንቅፋት አንድ ጊዜ መትቶህ አልፈኸው ሄደህ ድጋሚ ከመታህ . . . . . ይባላል ታዲያ እውነትም እንደ አባባሉ አልፈነው የመጣነው እሾህ ከሆነ እየወጋን ያለው የማነው ስህተቱ? ቤተክርስቲያን ምንም በፈተና ውስጥ የምትኖር ነች ቢባልም ባለፉት አርባና ሃምሳ አመታት የገጠማት ፈተና ግን ከውስጧ ባሉ ልጆቿ የሚነሳ ሆኖ ለውጭ ጠላትም በር እየከፈተ ቤተክርስቲያንን ያለስሟ መጥፎ ስም የሚሰጡ ሰዎች እንዲበረክቱ ምክንያት የሆነ ነው።

ለቤተክርስቲያን ፈተና መብዛት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ ማውጣት መድኃኒቱን ለማግኘት መፍትሄ ይመስለኛል "ህመሙን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም" እንደሚባለው ወደንም ሆነ ሳንፈልግ ችግሮቻችን ላይ እርምጃ ለመውሰድ መነሳት ካልጀመርን ሃዘንና ለቅሶ መከራን ይጨምራሉ እንጅ መፍትሄ አያመጡም።