ሁለት የተለያየ ባህርይ ያላቸው ጓደኛሞች ነበሩ ይባላል አንዱ የነቃ እና ፈጣን ሲሆን ሌላኛው ግን ፈሪ ከመሆኑም በላይ አስተዋይነት የጎደለው ነበር። መንገድ ሲሄዱ ይመሽባቸውና ማደሪያ ባለማግኘታቸው አጥር ተጠግተው ይተኛሉ ቆይቶም አንድ ድምጽ ያነቃቸዋል በዚህ ጊዜ ያ ፈጣንና ንቅ የሆነው ሰው ያንን ድምጽ እየሰማ መተኛት አልቻለም ስለዚህ ነቃ ብሎ ማጣራት ፈለገ። ነገር ግን ያ ድምጽ ከሱ ይልቅ ለጓደኛው የቀረበ መሆኑን ስለአረጋገጠ ሊቀሰቅሰው አሰበ ጓደኛው ግን ምንም እንዳልሰማ ድምፁን አጥፍቶ ተኝቶ ነበር በዚህ ተገርሞ ይቀሰቅሰውና ይህ የምሰማው ድምፅ ምንድነው? ለመሆኑ ይሰማሃል? ይለዋል እሱም መልሶ አዎ ይሰማኛል ዝም ብለህ ተኛ ይለዋል። ጓደኛውም በመገረም ታዲያ እንዴት ዝም ብለህ ተኛህ? ለመሆኑ የምን ድምፅ ነው? ይለዋል በዚህ ጊዜ ቆጣ ብሎ ጅቡ የኔን እግር እየበላ ነው ድምጽ አታሰማ ዝም ብለህ ተኛ አለው ይባላል:: ይህ ሞኝ ሰው አያ ጅቦ እግር በልቶ ሲጨርስ ወደ ጭንቅላት እንደሚመጣ ማሰብ አልቻለም:: ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ፈርጥ ጌጥ የካህናት አክሊል የሆኑ ምእመናንን ሰውነት የቆራረጠ ሰይፍ ነገ ዛሬ ዝምታን የመረጡ የቤተክርስቲያን መሪዎችን የሚምር ቢሆን መልካም ነበር ነገር ግን የሰይፍ ባህርይው መቁረጥ መቆራረጥ ነው ይህ ጽዋ እኛ ዘንድ ሳይመጣ ልንነቃ ያስፈልጋል:: ስለዚህ መቆሚያችን ምርኩዛችን ድጋፋችን ምእመናን በሚዘገንን ሁናቴ እየተገደሉ ዝምታን መምረጥ ለመኖር እግር አያስፈልገኝም እንደማለት ነው::
Wednesday, August 5, 2020
ካለፈው መማር ለምን አቃተን?
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሁን እንዳለንበት የሚያሳፍር ታሪክ ይኖራል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ምክንያቱም የተማረው ካልተማረው በታች የሚያስብ ሆኖ ተገኝቷል። ባለጸጋው ከድሃው በታች ሲያለቅስ ታይቷል። በዳዩ ከተበዳዩ በላይ እሮሮ ሲያሰማ ታይቷል። መሪው ከተራው ህዝብ በላይ መብቴ ጎደለ ሲል ተሰምቷል። ሁሉ የተሰጠው በእጁ ያለውን ማጣጣም አቅቶት ሲያለቅስ ታይቷል። ይሉኝታ የሚባል ነገር ጠፍቶ ሁሉ ለኔ ይሁን ሌላው ግን ምንደኛ መሆን አለበት የሚል ሰው በኢትዮጵያ ምድር በጉልህ ታይቷል። ታዲያ እንደዚህ ዘመን ነውረኛና አሳፋሪ ጊዜ ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት አይከብድም?
በ1998 ዓ.ም. በጅማ በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተሠዉ ምእመን
የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ክፉ ባህርያት ተዘርተው፣ በቅለው፣ ተኮትኩተው፣ ለምልመው፣ አብበው እስኪያፈሩ ድረስ እያየየ እየሰማ ምናልባት በጎ ዘመን ይመጣ ይሆናል በማለት አብዛኛው ዝምታን መርጦ ኖሯል በመሆኑም ይሆናል ያለው ሳይሆን መሆን ያለበት ሆኖ ፍሬውን መብላት ግድ ሆኖበታል።
አሁንስ ምን ተማርን? እየተዘራ ያለው እስኪበቅል እንጠብቅ ወይስ ያለፈው ይብቃ ብለን ወደ ማስተዋል ተመልሰን ለትውልድ ከሚተላለፍ ደዌ ኢትዮጵያን እንታደግ? እሳቱም ውሃውም በእጃችን ነው። የሚጠቅመንን መምረጥ ከእኛ አልፎ ለልጆቻችን የሚተርፍ ሀገር እንዲኖረን ያስችላል።
የእኛ ትልቁ ችግር የሚጀምረው የተፈጥሮን ሥርዓት ባለመቀበል አንድ ሰው በተወለደበት ሥፍራ መጤ ነህ ከማለት ነው። እኔ ብቻ ልኑር የሚለው ፈሊጥ ሰይጣናዊ ከመሆኑም በላይ ሞትን ወደ ራስ መጋበዝ ነው። እኔ ልኑር ስል ሌላውም ለመኖር የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ካልተገነዘብኩ እንደ እኔ ያለ ጭፍን ከየት ይገኛል? ከዚህም በላይ ደግሞ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለው የሰይጣን ፈረስ ሁኗል ማለት ነው። ቃየል ወንድሙን አቤልን በጥቅም በመግደሉ የሰይጣን ወንድም ተብሏል ዘፍ 4፥8
Subscribe to:
Posts (Atom)