Monday, August 6, 2018

ፈጥኖ ደራሽ መንግሥት እንዲኖረን እመኛለሁ

ይህን ጽሁፍ ስጽፍ የዶ/ር አቢይን ጥረትና ድካም ከንቱ በማድረግ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ አደራ እላለሁ። በሱማሌ ክልል የደረሰውን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊት በማየትና በመስማት ይህን ጻፍኩ።  በሀገራችን ለምን ተመሳሳይ ስህተቶች እንደሚሰሩ እስከ አሁን በግሌ የተረዳሁት ነገር የለም። የትላንቱን እየኮነንን ለምን ዛሬ ከትላንቱ የባሰ ጥፋት እንዲጠፋ እድል እንደምንሰጥም አልገባኝም። በኢትዮጵያ ምድር የሰው ህይዎት ክቡር መሆኑ ታምኖ ጥበቃ ሲደረግለት ማየት በጣም ነው የናፈቀኝ።

ዶ/ር አቢይ ከብዙዎቻችን በላይ ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው በግሌ አምናለሁ ነገር ግን የያዙት የፍቅርና የአንድነት ጉዞ እንዳይደናቀፍ በክልሎች አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችን ለማስወገድ የነደፉት እስትራቴጂ ፍጥነት ያንሰዋልና ትኩረት ቢደረግበት መልካም ነው። በሌሎች ሀገሮች ያለውን የችግር አፈታት ስናይ በእኛ ሀገር የሚሆነው ሆን ተብሎ የሚደረግ እስኪመስል ድረስ ግራ የሚያጋባ ነው። በጦር መሳሪያ የተደገፉ ጭፍጨፋዎች እየተካሄዱ፣ የህዝብና የሃይማኖት ተቋማት እየወደሙ ስናይ መንግሥት አልባ ሀገር ብንል ማነው የሚፈርድብን? ምክንያቱም የመንግሥት ሥራና ኃላፊነት ህዝብንና የህዝብ የሆነውን ሁሉ መጠበቅ ሆኖ ሳለ የመንግሥት አካላት የተሳተፉበት አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸም አይተናላ፦ አጥፊዎች የሚፈልጉትን ካወደሙ በኋላ መግለጫ መስጠት የመንግሥት ተግባር ነው ብየ አላምንም ይህን አጥፊዎቹም ያደርጉታል። መንግሥት ኃላፊነቱ ቢቻል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከአጥፊዎች ቀድሞ መፍትሄ ማበጀት፣ ይህ ባይሆን እንኳን ከሌላው ፈጥኖ በመድረስ መታደግ ቀዳሚ ተግባሩ መሆን  ይኖርበታል። ዓለም አቀፍ ሚዲያ እያስተጋባ የሀገሪቱ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ ዝምታን ከመረጠ ከህዝብ ጆሮ ያልደረሰ ችግር እንዳለ ያሳያል። ከዚህ በፊትም እንደተባለው ሀገሪቱን እንደ ገና ዳቦ ሸንሽኖ፣ የጥላቻና የዘረኝነትን ካባ አልብሶ፣ የመገናኛውን ድልድይ ሰባብሮ የጣለው ሀገሪቱ የምትመራበት ሥርዓት በመሆኑ አፋጣኝ ፍተሻ ቢደረግበት መልካም ነው። ይህ ካልሆነ መንግሥት ምንም በጎ ሰራሁ ቢል ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው።  የቤተክርስቲያናችን አባቶች ይቅርታ ይደረግልኝና የምለው አለኝ።  ካህናት ተጨፍጭፈው በእሳት ሲቃጠሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ሲወድሙ፣ ህዝብ ከቅየው ተፈናቅሎ በረኃብ በችግር ሲንገላታ ድምጻችሁን ማሰማት ካልቻላችሁ ቤተ ክህነት እንደ ተቋም አለ ማለት ይቻላልን?

መ/ሃይማኖት ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ
St louis Missouri

2 comments:

  1. ቀሲስ ያሰፈሩት ሀሳብ ተገቢና ወቅታዊ ነው። ለሰላምና ለፍቅር የሚደረግ ጉዞ ከምንም በላይ ብዙ ታገሽነትና አስተዋይነትን ይጠይቃል። ሆኖም ግን አሁን በተከሰተው ችግር መንግስት እነደ መንግስት ሕዝቡን የመጠበቅና የማረጋጋት ሀላፊነት ሊኖረው ይገባል። ይህንን ሊያደርግ ወይም ከአቅም በላይ የሆኑ ከባድ ማነቆዎች ካሉበት ለሕዝብ ሳይደበቅ ይፋ መውጣት አለባቸው። ተሸፋፍኖ ካለፈ በኋላ ላይ የሚያስከትለው ችግር ከአሁኑ በላይ የከፋ ይሆናል።
    አብርሃም
    አመሰግናለሁ

    ReplyDelete
    Replies
    1. አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር በጎውን ያድርግልን።

      Delete