ጥንት አባቶቻችን አንድ ነገር ለማድረግ ሲነሱ ከመነሻው መድረሻውን የሚያውቁበት ልዩ ጸጋ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ ከመጀመራቸው በፊት ፍጻሜው የት ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ። በመሆኑም በመንገዳቸው ብዙም ፈተና ቢገጥማቸው ማምለጫውን ያዘጋጃሉ። ስለዚህ ብዙ ከባድ ነገሮችን አልፈው ስኬታማ የሆኑባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።
እኛጋ እያስቸገረን ያለው ነገር ይህ ነው። ምንም ነገር ሳንጀምር መጨረስ እንፈልጋለን። ,, የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ,, እንዲሉ ዘለን አናቱ ላይ መውጣት እንፈልጋለን። በዚህም የተነሳ በድካማችን ውስጥ ስኬት አልባ እንሆናለን። ከመጀመር በፊት ፍጻሜውን መገመት ይገባል። ሁሉ ነገር እና እንዳሰብነው ይሆናል ብሎ መገመት ስህተት ነው። በተለይ የብዙኃን የሆነ ነገር ላይ ውሳኔ ስንወስን በአራቱም አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን የብዙዎች ነች። ይህን የሚገነዘቡ ግን ጥቂቶች ናቸው። አንዳንዶች ብዙ ገንዘብ ስለከፈሉ፣ አንዳንዶች ብዙ ዘመን ስለቆዩ፣ አንዳንዶች ብዙ ቲፎዞ ስላላቸው ለቤተክርስቲያን እራሳቸውን ብቸኛ አካል አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ቤተክርስቲያን እንኳን በ40 በ80 ተጠምቆ ልጅነትን ያገኘባት ይቅርና ለአህዛብም እንኳን በተስፋ እናታቸው ናት። አሁን ሁሉም አትኩሮ ሊመለከተው የሚገባ ይህ ጉዳይ ነው። የቤተክርስቲያን ልጆች ከካህናት እስከ ምዕመናን ድረስ እንደ ባይተዋር ምክንያት እየተፈለገ የሚባረሩበት አካሄድ መስተካከል አለበት ። በእናቱ ቤት ባይተዋር እየተደረገ የሚታይ ልጅ መኖር የለበትም። እድሜ ዘመናቸውን መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰም ከሃገር ሃገር ሲባዝኑ ኑረው በተማሩት ትምህርት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሲመጡ ተገቢውን ክብር ማግኘት አለባቸው። የምናውቀውን ሁሉን ብናወራው የማያንጽ ስለሆነ ማለፉ ይሻላል።