የዘመናትን መለዋወጥ ስናነሳ ባለጊዜዎችን ማውሳታችን አይቀሬ ነው። እስቲ ሁላችንም አንድ ነግር እራሳችንን እንጠይቅ, ዘመን የሚሄደው ወደ ፊት ነው ወደ ኋላ? መልሱ ሊሆን የሚችለው ወደ ፊት ነው። የሚገርመው ነገር ግን ዘመን ወደ ፊት ሲሄድ ባለ ዘመኖች ወደ ኋላ መሄዳቸው ነው።
ወደ ፊት መሄድ ብርታትን ፣ ውጤትን፣ ድል አድራጊነትን፣ አሸናፊነትን ወ ዘ ተ ሲያመለክት ወደ ኋላ የምንለው ደግሞ መሸነፍን፣ ኋላቀርነትን፣ ውርደትን፣ ያሰቡት ቦታ መድረስ አለመቻልን፣ የተፈጥሮን ሂደት አለመከተልን ወ ዘ ተ ሊያመለክት ይችላል። ይህን ስናስብ ምን ያህል ወደፊት እንደተጓዝን እራሳችንን ስንጠይቅ ዘመን ተጉዟል እኛ ደግሞ ተጎትተናል። እውነት ነው ዘመን ቆሞ አይጠብቅም ይጓዛል። ትልቁ ችግር ብቻውን መጓዙ ነው።
የሰው ልጅ የፍቅር ጉዞ፣ የመተባበር ጉዞ፣ የመተዛዘን ጉዞ፣ የመደጋገፍ ጉዞ፣የመተሳሰብ ጉዞ፣ የመቻቻል ጉዞ፣ የመከባበር ጉዞ ወዘተ አንድ ቦታ የቆመ ይመስላል። ታዲያ ምን ዋጋ አለው ዘመን ብቻውን ቢሮጥ። ጭነቷን እንደጣለች አህያ ቢፈረጥጥ ምን ዋጋ አለው?
በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ዘመን ሁለት ጊዜ አዲስ ዓመትን እናከብራለን የራሳችን እንደተጠበቀ ሆኖ ምዕራባውያንና አውሮፓውያን ቅር እንዳይላቸው የነሱንም አዲስ ዓመትም በድምቀት ማክበር ከጀመርን ሰነባብተናል። ለነገሩ ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ ስለተባለ በሌሎች የደስታ ቀን አብሮ መደሰት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባህል ነው። ችግሩ የራስን ትቶ በሰው ላይ ማፍጠጥ መሆኑ ግን ትዝብት ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው።
በአንድ ወቅት በሃገራችን ያሉት በዓላት ስለበዙ መቀነስ አለባቸው እየተባለ በከፍተኛ ሁኔታ ቅስቀሳ ይደረግ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። እንደውም ሰርግና ቁርባን ሲደግሱ የተገኙ የገንዘብ መቀጫ እንደተጣለባቸውም ሰምተናል። ዛሬ ላይ ሲታይ ግን በሃገራችን ያሉት መንፈሳዊም ሆነ ባህላዊ የደስታ በዓላቶቻችን የህብረተሰቡን ኑሮ የሚጎዱ ሆነው ሳይሆን። በምዕራባውያን ባህሎች እንዲቀየጡ ከመፈለግ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ገና፣ ጥምቀት ፣ፋሲካ ፣መስቀል እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ለብዙ ዘመናት የኖሩት ሰርግና ሙታንን በጸሎት ማሰብ የመሳሰሉት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን የህብረተሰባችንን የኑሮ እድገት ወደ ኋላ እንዳስቀሩት ምሁራን ነን በሚሉት ወገኖቻችን ሳይቀር ሲገለጹ ሰምተናል። ከኛ በእውቀት ይሻላሉ የምንላቸው ሃገርን የሚመሩ ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው ሰዎች ከተናገሩ ተቀባይነት ማግኘቱ የግድ ነው። ነገር ግን እውቀትም ሆነ ኃላፊነት ላይ መቀመጥ ወደ ፊት የማያራምድ ከሆነ ከንቱ ነው። የአንድ ሃገር ዳር ድንበር ተከብሮ ፣ ህዝቡ በሰላም መግባት መውጣት ከቻለ አንድ ውጤት ነው። ነገር ግን በውስጡ ያለው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቱ ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ የተቻለ እንደሆነ ነው ስኬት የሚባለው።
እናት ምንም ጊዜ ቢሆን እናት ነች። ዘመን ጠብቆ የሚሸራረፍ ፍቅር የማይሰጣት ነች። አንዳንዶች ለእናታቻው ከእድሜያቸው ተቀንሶ ቢሰጥ ይፈቅዳሉ። እውነተኛ ያልሆነ ልጅ ( ምንደኛ ) ካልሆነ በስተቀር የእናቱ መልክ እንዲጠፋ የሚፈልግ ልጅ የለም። ችግር ካልሆነበት በስተቀር ጉስቁልናዋን ማየት አይፈልግም። የእናትነት ትርጉም ይህ ሆኖ ሳለ እውነተኛው መልኳን አጥፍቶ አርቴፊሻል መግጠሙ መልኳን ያጠፋዋል እንጅ ውበት አይጨምርም። ትልቁ ችግር ደግሞ የቀድሞ ውበቷ ከጠፋ ተመልሶ የማይገኝ በመሆኑ ነው። በህክምና የሰው አካል የሚቀይሩ ሃኪሞች የተጎዳ አካል ላለው ሰው የጤነኛ ሰው አካል ለመቀየር ሲጀምሩ ያስፈርሙታል። ምክንያቱም አዲሱ የሚገጠምለት አካል ምናልባት ከሰዉነቱ ጋር ባይዋሃድ ወይንም ደግሞ እንደተጠበቀው መስራት ባይችል ሊሞት ስለሚችል ሃላፊነቱን እንዲወስድ ያስፈርሙታል ። ወደ ነበረበት መመለስ ስለማይቻል ማለት ነው። እኛም እያደረግን ያለነው ከዚህ የተለየ አይደለም ። ዛሬ እየናቅን የጣልነው ባህል ነገ ተመልሰህ አካል ሁን ብንለው ሊሆን አይችልም። ነገ የሚኖረው ሊላ ትውልድ ነውና።
የተለያዩ ሃገራትን የታሪክ አጠባበቅ ስንመለከት። እንደነ እስራኤልና ግብጽ የመሳሰሉት ሃገራት እንኳን የሚያምኑበትን ይቅርና የማያምኑበትን ታሪክ እንኳን ተጠብቆ እንዳለ ሳይሸራረፍ ለትውልድ መተላለፍ አለበት የሚል ህግ አላቸው። ስለዚህ ምንም እንኳን የፈቀድነውንና ያመንበትን፣ ዓለም የተስማማበትን ማንኛውንም ባህል የመከተል የሁሉም መብት መሆኑን ባምንም ኢትዮጵያ ያላት ለረጅም ጊዜ ተጠብቆ የኖረው ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት በትውልዱ ዘንድ ተጠብቆና ተከብሮ መኖር አለበት የሚል ጽኑዕ አቋም አለኝ።
ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያድርሰን
No comments:
Post a Comment