ከእለታት አንድ ቀን የዚህን ሰው ታሪክ የማያውቅ ከሩቅ አካባቢ ለስርቆት የተሰማራ ሰው በድንገት በቤቱ ገባ። ሌባው ተስፋ አድርጎ የነበረው ገንዘብ እንኳን ባላገኝ ያገኘሁትን ንብረት ይዤ እወጣለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን ቤቱ ውስጥ አንዳች የሚታይ ንብረት አልነበረም። ሌባውም ያልጠበቀው ነገር ስለገጠመው እየተደነቀ ወደሚቀጥለው ክፍል አመራ። ይኸኛውም ክፍል የተለየ ነገር አልነበረውም። የሚለየው ከግርግዳው ጥግ ላይ አንድ አሮጌ ፍራሽ ተዘርግቷል። በላዩም ላይ ያለቀ ብርድ ልብስ የለበሰ ሰው ተኝቶበታል። ባየው ነገር ተስፋ የቆረጠው ሌባ ወደ ሌሎች ክፍሎችም ቢሄድ የተለየ ነገር እንደማይገጥመው በመገመት ከዚያ ቤት መውጣት እንዳለበት አሰበ። ወደኋላው ተመልሶ በገባበት መስኮት ለመውጣት ሲሞክር ያ ተኝቶ የነበረው ሰው አፈፍ ብሎ በመነሳት ተወርውሮ አነቀው። ሌባውም በመደናገጡ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ለመውጣት ሞከረ ነገር ግን አልቻለም ተያይዘው ሁለቱም ከመሬት ላይ ወደቁ።
ሌባውም በፍርሃት ተውጦ ተርበተበተ። ምንም አማራጭ እንደሌለው ስላወቀ ጌታየ ይቅርታ አድርግልኝ እርቦኝ ነው የምበላው ስለሌለኝ ነው ድሃ ነኝ በሽተኛ ነኝ። እንዳትጎዳኝ ሰበብ እሆንብሃለሁ በማርያም በገብርኤል በመድኃኔዓለም የዛሬን ማረኝ እያለ እየጮኸ ይናገራል። ያ ሰው ግን አንዳች ነገር አልተናገረም ነበር። ባጠገቡ ያለውን ክብሪት አንስቶ ከመቅረዙ ላይ ያለውን ሻማ ለኮሰ። አሁን ፊት ለፊት ሁለቱም መተያየት ጀመሩ። ሌባው የጠበቀው ዱላም ሆነ ሰውን የሚጎዳ መሳሪያ በሰውየው እጅ አልነበረም። የሚቀጥለውን ለማየት ሌባው በዚያው በወደቀበት ሆኖ ሰውየውን አትኩሮ ይመለከተው ጀመር። ጌታየ ህመምተኛ ነኝ የዛሬን ማረኝ ብሎ መናገር ሲጀምር በእጁ ምልክት ሰጥቶ አስቆመው። ሁለቱን እጆቹን ዘረጋለት ተነስ ብሎም ከወደቀበት አነሳው። አቅፎም ሳመው ። አይዞህ አትፍራ እኔ ባንተ ላይ ምንም ላደርግ ስልጣን የለኝም። እውነትህን ነው አምንሃለሁ ስለቸገረህ ነው ወደ ስርቆት የገባኸው። ለኔ ግን ዛሬ ያንተ ወደ ቤቴ መምጣት ትልቅ ትርጉም አለው። ዘመድ ወገን ጓደኛ በናቀኝና በጠላኝ ሰዓት ከሰው እኩል ቆጥረኸኝ ወደ ቤቴ ስለመጣህ አመሰግንሃለሁ። በዓለም ላይ ከሰው ወገን ብቸኛ ዘመዴ አንተ ነህ። ብሎ ደጋግሞ አቅፎ ሳመው። ዛሬ በዚህ ሌሊት ከፈጣሪየ ጋር እየተሟገትኩ ነበር። እስከመቼ እንደተናቅሁ እኖራለሁ መገፋቴን መራቆቴን ተመልከት እያልኩ ወደ አምላኬ ስናገር ነበር። ከንግግሬም አንዱ ፈጣሪየ አንተም እንደሰዎች ረሳኸኝ? ዛሬ ህይዎቴን የሚለውጥ ነገር ካላሳየኸኝ በስምህ የታተምኩበትን የአንገት ክሬን እበጥሳለሁ ብየ ተናግሬ ነበር። ከአምላኬ መልስ በምጠብቅበት ሰዓት አንተ ወደቤቴ ገባህ። መቸም እግዚአብሔር በአካል ወደኔ አይመጣ ስለዚህ ባንተ በኩል ለኔ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት እንዳለው ተረዳሁ። ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ተስፋየ ለምልሟል. ለኔ ከሰው መቆጠር ብቻ ነበር የሚያስፈልገኝ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ሰው ነኝ። ቀድሞ ሃብት ንብረት እንዴት እዳፈራሁ አውቃለሁ አሁንም እግዚአብሔር ከኔ ጋር ነው እንደቀድሞው ሰርቼ አገኛለሁ። የዚያን ጊዜ የናቁኝ ሁሉ ያከብሩኛል አለ።
ከሰው መቆጠር ባለፈ ሃገር የሚመሩ፣ ቤተክርስቲያን የሚመሩ፣ ህዝብን በተለያየ መንገድ የሚያገለግሉ፣ ይኸን ያስቡት ይሆን? እንደ ሰው ከመቆጠር አልፎ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ አስተዳዳሪና አገልጋይ ማድረጉ እጅግ አይደንቅም? እንደሰው አለመቆጠርም አለና በተሰጠን ጸጋ እግዚአብሔርን እናክብርበት።
ከሰው መቆጠር ባለፈ ሃገር የሚመሩ፣ ቤተክርስቲያን የሚመሩ፣ ህዝብን በተለያየ መንገድ የሚያገለግሉ፣ ይኸን ያስቡት ይሆን? እንደ ሰው ከመቆጠር አልፎ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ አስተዳዳሪና አገልጋይ ማድረጉ እጅግ አይደንቅም? እንደሰው አለመቆጠርም አለና በተሰጠን ጸጋ እግዚአብሔርን እናክብርበት።
No comments:
Post a Comment