Friday, June 29, 2012

ኮሶ አረህ


ይህ ቦታና አካባቢ ለአዲስ አበባ ቅርብ ቢሆንም ከመልክአምድራዊ አቀማመጡ ገደላማነት የተነሳ ምንም አይነት የዓለም ስልጣኔ ሊደርስበት አልቻለም። ነገር ግን አስቀድሞ የተዘረጋው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱ እጅግ ሰልጥነናል ከሚሉት አካባቢዎች የተሻለ ነው። ለምሳሌ በአካባቢው አንድ ጸጉረ ልውጥ ሰው ቢታይ ሁሉም ህብረተሰብ በአይነ ቁራኛ ስለሚከታተለው ምንነቱ በቅጽበት ይታወቃል። በዚህ የተነሳ እስከ አሁን ድረስ በአካባቢው ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውጭ አንድም የእምነት ተቋም አይገኝም። አንድ የሌላ እምነት ሰው በተለያየ ምክንያት ወደ አካባቢው ቢመጣ ከተወሰኑ ቀናት ውጭ እንዲኖር አይፈቀድለትም። መቆየት ከፈለገ ስርዓተእምነቱን ተምሮ እምነቱን ተቀብሎ የመኖር ግዴታ አለበት። ካልፈለገ አይገደድም በሰላም ወደመጣበት የሚገባውን አሸኛኘት ይድረግለታል።


     አስታውሳለሁ የዛሬ 27 ዓመት ገደማ የ77 ዓ/ም ድርቅ በፈጠረው ችግር ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ህዝቦች በፍልሰት ወደተለያየ ቦታ ይሄዱ ነበር። የተወሰኑ ከወሎ አካባቢ የመጡ ቆዳ በመፋቅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ወደዚህ አካባቢ መጥተው ነበር። ለተወሰኑ ቀናት ለጊዜያዊ ችግራቸው የሚሆን እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ የመጡበት አካባቢ የት እንደሆነ እና አምልኮታቸው ምን እንደሆነ ጥያቄ ቀረበላቸው ። እነሱም የመጡበትን አካባቢና እምነታቸውም እስልምና መሆኑን ተናገሩ። በአካባዊው ስርዓት መሰረት ወይ የአካባቢውን ሃይማኖት ተቀብለው እንዲኖሩ ወይንም ደግሞ የሚፈልጉትን እርዳታ ካገኙ በኋላ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ በአግባቡ ጥያቄ ቀረበላቸው። እነሱም ሃይማኖቱን የሚያስተምረን ስርዓቱን የሚያስረዳን አዋቂ ሰው ይመደብልን በማለታቸው ካሉት መምህራን ተመድቦላቸው የክርስትናን እምነት በሚገባ ከተማሩ በኋላ በራሳቸው ጥያቄ አቅራቢነት ስርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው ኑሯቸውን በዚያው አድርገዋል። ሌሎች ብዙ ወገኖቻቸውንም ወደዚሁ እምነት እና አካባቢ እንዲመጡ አድርገዋል።

     ስለዚህ አካባቢ ካነሳሁ ዘንዳ ጥቂት ማለት እምፈልገው ነገር አለ። ከላይ እንደገለጽኩት በአካባቢው ገደላማነት ምክንያት በውስጡ የሚገኙት ቅዱሳን መካናት በከተማው ህዝብ ዘንድ ሊታወቁ አልቻሉም። ነገር ግን ታላላቅ ቅዱሳን አባቶቻችን የረገጡትና በአካባቢው ታላላቅ ተአምራት ያደረጉበት አካባቢ ነው። እነጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አቡነ ዜናማርቆስ፣ አቡነ ቀውስጦስ ወ ዘ ተ ። በተለይ ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ በዚሁ አካባቢ ታላቅ ተጋድሎ እንደፈጸሙ በገድላቸው ላይ ተጽፎ ይገኛል። እስከአሁንም ድረስ በዚሁ አካባቢ በሚገኘው ጸበላቸው ብዙ ህሙማን ከደዌያቸው ይፈወሳሉ። አጋንንት የሳቸው ስም ሲጠራ ካለመከራከር ካደረባቸው ሰዎች ላይ ለቆ ይሄዳል። ጻድቁ በህይዎተስጋ እያሉ አካባቢውን ከአጋንንት አሽክላ ነጻ አውጥተው ህዝቡንም በቃል ኪዳን በአባትነት ከእግዚአብሔር ተቀብለዋል። በዚህ የተነሳ እስከአሁን በዚያ አካባቢ ሌላ እምነትም ሆነ አምልኮ ባእድ አይገኝም።

        ጻድቁ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ በዘመኑ የነበረው አላዊ ንጉስ መከራ አጽንቶባቸው በልዩ ልዩ ስቃይ ካንገላታቸው በኋላ ኮሶ አረህ በተባለው ቦታ ላይ አንገታቸውን በሰይፍ እንዲቀሉ አድርጓል። በዚህ ጊዜ ከተራራው ላይ ደማቸው ሲፈስ ሌሊቱ ብርሃን ሆኗል። በዚህም የተነሳ እስከዛሬ ድረስ አካባቢው ቀን በመባል ይጠራል። ደማቸው እንደጸሃይ አብርቶ ሌሊቱን ወደቀን በመለወጡ ምክንያት ቀን የሚለውን ስያሜ አግኝቷል። ሰማእትነት በተቀበሉበት ቦታ ላይ ለመታሰቢያቸው በእመቤታችን እና በእሳቸው ስም ቤተክርስቲያን ተሰርቶላቸዋል። ቀን ማርያምና ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ በመባል ይታወቃል። አካባቢው ሁሉ የተሰየመው ጻድቁ ሰማእትነት በተቀበሉበት ሰዓት የተፈጸሙትን ተአምራት የሚገልጽ ነው ለምሳሌ ከቀን ቀጥሎ የሚገኘው አካባቢ ጥቁር ዱር ይባላል። ይህንን ስም ያገኘው ጻድቁ ሰማእትነት ሲቀበሉ ሌሊቱ ቀን ሲሆን የሌሊቱ ብርሃን እስከዚህ አካባቢ ይደርስ ነበር ። ከዚያ ቦታ ጀምሮ ያለው ግን የጨለማ መጋረጃ መስሎ ይታይ ስለነበር ጥቁር ዱር የሚለውን ስያሜ አግኝቷል። ደማቸው በፈሰሰበት ቦታ ጸበል ፈልቆ እስከዛሬ ድረስ ከተለያየ ቦታ ሰዎች በቃሬዛ በሰው ሸክም እየመጡ ድነው በእግራቸው አምላከ ጻድቁ ቀውስጦስን እያመሰገኑ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። 

ከዚህም ሌላ በአቅራቢያው የሚገኙ ብዙ አብያተክርስቲያናት አሉ። እግዚአብሔር ፈቅዶለት ቦታውን ለመርገጥ የታደለ ሰው በቅርብ እርቀት የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት ተሳልሞ የመምጣት እድል አለው። በተረፈ ሰፊውን የአካባቢውንና የቅዱሳን መካናቱን ታሪክ በቦታው ተጘኝቶ የተረዳ ሰው እድለኛ ነው እላለሁ። እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ የሰራውን ስራ በአይን መመልከትና በእግር መርገጥ እምነትን አጽንቶ ለመኖር ይጠቅማል። ወደቦታው ለመሄድ ለሚፈልጉ ሁሉ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ሊባኖስ የሚወስደውን መንገድ ተይዞ ሲኬድ መልከጡሪ (ሙከጡሪ) ሲደርሱ ወደቀኝ ታጥፈው ለሚ ከተማ ለመድረስ 15 ኪሎ ሜትር ሲቀረው ይወረዳል። ከዚያም አፋፉ ላይ ሆኖ በዙሪያው ያሉትን አብያተክርስቲያናት ማየት ይቻላል። ከመኪና የሚወረድበት ቦታ ተግባሪ ይባላል። በዚሁ አካባቢ የጻድቁ የአቡነ ቀውስጦስ ቤተክርስቲያን ከገደሉ አፋፍ ላይ ይጘኛል። ከላይ የገለጽኩትን ቀን ማርያምን ከዚሁ ቦታ ሆና መመልከት ይቻላል።  ከቤተክርስቲያኑ በቅርብ በሚገኘው ገደል ስር ጻድቁ ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ሊቃውንት ይናገራሉ። ቦታውም ኮሶ አረህ ተብሎ ይጠራል። የጻድቁ የአቡነቀውስጦስ አጽም ያረፈው ግን ከላይ በገለጽኩት ቀን አባ በሚባለው ቦታ ነው። ብዙ ድውያን የሚፈወሱበት ጸበላቸው ያለው ከመቃብራቸው አጠገብ ነው።



  የቅዱሳን አባቶቻችን በረከት በሁላችንም ላይ ይደር 




No comments:

Post a Comment