Wednesday, February 25, 2026

ሰባቱ የኃጢአት ራሶች

፠ ሰባት ራሶች፦ የተባሉት በመጨረሻው በሐሳዊ መሲህ ዘመን የሚፈጸሙ ሰባቱ ዋና ዋና ኃጢያቶች ናቸው። እነዚህም 7ቱ አርዕስተ ኃጣውዕ ወይም 7ቱ የኃጢአት ራሶች ይባላሉ!

እነርሱም፦👇
1) ኃጢያተ አዳም (ወይም የአዳም ኃጢያት
2) ቅትለተ አቤል (የአቤል መገደል)
3) ጥቅመ ሰናዖር (የሰናዖር ህንፃ)
4) ኃጢያተ ሰዶም (የሰዶምና ጎሞራ ሰዎች ኃጢያት)
5) ኃጢያተ እስራኤል (የእስራኤላዊያን ኃጢያት)
6) ቅትለተ ዘካርያስ ካህን (የዘካርያስ ካህን መገደል)
7) ሞተ ወልደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት) ናቸው።
---------------------------//----------------------------


1) ኃጢያተ አዳም፦
~~~~~~~~~~~~
ይህ ማለት የአዳም ኃጢያት ማለት ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም አምላክነትንና ፈጣሪነትን ስለሻተና ስለተመኘ አትብላ የተባለውን "ዕጸ በለስን" በላ። በዚህም ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ ከክብር ቦታ ከገነት ተባርሮ ወጣ። አሁንም በዚህ በመጨረሻ ዘመን የሚነሳው ይህ ሐሳዊ መሲሕ "እኔ አምላክ ነኝ ፤ እኔ ፈጣሪ ነኝ ፤ ለእኔ ስገዱ" እያለ የሚመጣ ሰው ነው። በሞተ-ወልደ እግዚአብሔር ተደምስሳ የነበረችውም የአዳም ኃጢያት (አምላክነትን መሻት) በዚህ በሐሳዊው መሲሕ ዘመን ለመጨረሻ ጊዜ አይላ ትፈፀማለች ማለት ነው። ዘፍ 3:1
በምንም የሚያስታችሁ አይኑር ፤ ክህደት ሳይመጣና የአመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያቺ ቀን አትመጣምና።
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ
ለሁሉም እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ የሚል በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሚቀመጥ ራሱንም እንደ እግዚአብሔር የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው።" 2ኛ ተሰ 2:3-5
----------------------------//--------------------------------
2) ቅትለተ አቤል፦
~~~~~~~~~~~

Sunday, February 1, 2026

ጾመ ነነዌ

ጾመ ነነዌ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዷ ስትኾን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ይህቺ ጾም የምትጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሟ የምትጀመርበት ቀን ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡ ቀኑ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፋ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ቀን ይረዝማል፡፡ ጾመ ነነዌ በእነዚህ ፴፭ ቀናት ውስጥ ስትመላለስ (ከፍ እና ዝቅ ስትል) ትኖራለች፤ ከተጠቀሱት ዕለታት አትወርድም፤ አትወጣም፡፡ በዚህ ዓመትም (፳፻፲፰ዓ.ም) ጥር ፳ ቀን ትጀመራለች፡፡

‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሚለው የጽሑፋችን ርእስ እንደሚያስረዳው ይህቺን የሦስት ቀን ጾም የጾሟት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው /ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪/፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የኾነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶባት ነበር /ዮናስ ፬፥፲፩/፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኀጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው /ሉቃ.፲፩፥፴/፡፡


ዮናስ የስሙ ትርጕም ‹ርግብ› ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናግሯል /፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩/፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል /፩ኛነገ.፲፯፥፲፱/፡፡ መድኀኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ኾድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል /ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪/፡፡

ተክለሃይማኖት ፀሐይ

እንኳን ለፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ስባረ አጽም የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

አበ ኩልነ አባ ተክለሃይማኖት አስተጋብአነ ለሥብሃተ እግዚአብሔር ( የሁላችን አባት አባ ተክለሃይማኖት እኛ ልጆችህን ዘወትር እግዚአብሔርን ለማመስገን የተጋን፣የነቃን፣ የበቃን አድርገን) ብሎ እንደተናገረው ዛሬ ምድረ ኢትዮጵያ ጻድቁ አባታችን በወንጌል ያረሰረሷት በፈተና ላይ ነችና ከጥፋት እንዲታደጓት ፈቃዳቸው ይሁንልን።

የኢቲሳ አንበሳ ተክልዬ ተነሳ
ወገንክን ታደገው ከኃጢአት አበሳ. . .

እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ የመረጣቸው ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን 1197 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ማለትም ‹‹አንዱ አብ ቅዱስ ነው አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ አመስግነውታል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ይኸውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ የወላጆቻቸው የቀድሞ ስማቸው ዘርዐ ዮሐንስና ሣራ ይባል ነበር፡፡

ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል የትውልዳቸው መሠረት ኢያሱ ለሌዋውያን ክፍል ትሆን ዘንድ ከለያት ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ ስማቸው የተጠቀሰው እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን የወንድማማቾች ልጆች ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ 61ኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ይኸውም እንዴት ነው ቢሉ ትውልዱ ከአዳም ጀምሮ በካህኑ አሮን በኩል የሆነውና የሌዋዊያን ሊቀ ካህን የነበረው የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከታቦተ ጽዮንና ከብዙ ሌዋዊያን ካህናት ጋር ሊቀ ካህን ሆኖ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አክሱም ተቀምጦ ኖረ፡፡ የኦሪትንም ሕግ እየዞረ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ ትውልዱም በአብርሃ ወአጽብሓና በአባ ሰላማ ዘመን እስከነበረው እንበረም የሚባለው ጻድቅ ድረስ ደረሰ፡፡ የእንበረምም ትውልድ ደገኛው ሕይወት ብነ በጽዮን ድረስ ደረሰ፡፡ ሕይወት ብነ በጽዮንም የደማስቆ ምድር ከሚሏት ከወለቃ ሀገር የመኮንን ልጅ የሆነችውን ወለተ ሳውልን አግብቶ አበይድላን ወለደ፡፡ አበ ይድላም በንጉሡ ድልዓዥን ዘመነ መንግሥት ለ150 ካህናት አለቃ ሆኖ በወለቃ ሀገር የክርስቶስን የወንጌል ሕግ እያስተማረ ብዙዎችን አጠመቀ፡፡ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ እያስተማረ መጥቶ በሸዋ ምድር ተቀመጠ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳነጸ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትንም ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹በሸዋ ጽላልሽ ተቀምጦ ሲያስተምርም በአንዲት ቀን እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ያጠምቅ ነበር›› በማለት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይመሰክርለታል፡፡



አበይድላ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር ከሸዋ ጽላልሽ ምድረ ዞረሬ ሚስት አግቶ ሀበነ እግዚእን ወለደ፤ ሀበነ እግዚእም በኩረ ጽዮንን ወለደ፤ በኩረ ጽዮንም ሕዝበ ቀድስን ወለደ፤ እርሱም ነገደ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ሕዝበ ቀድስም ብርሃነ መስቀልን ወለደ፤ እርሱም ዐቃቢነ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀልም ሕይወት ብነን ወለደ፤ እርሱም ሴትን ወለደ፡፡ ሴትም ወረደ ምሕረትን ወለደ፡፡ ወረደ ምሕረትም ዘካርያስን ወለደ፡፡ ዘካርያስም የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የሆኑ 6 ወንድማማች ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም እንድርያስ፣ አርከሌድስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብ፣ ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ዮናስ ናቸው፡፡ እንድርያስም ሳሙኤል ዘወገግን ወለደ፤ አርከሌድስም ሕፃን ሞዐን ወለደ፤ ዘርዐ አብርሃምም ታላቁን አኖርዮስን ወለደ፤ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብም ተክለ ሃይማኖትን ወለደ፤ ቀሲስ ዮሐንስም ዜና ማርቆስን ወለደ፣ ቀሲስ ዮናስ ደግሞ የፈጠጋሩን ማትያስንና ገላውዲዮስን ወለዳቸው፡፡ ገላውዲዮስም የመሐግሉ ቀውስጦስን ወለደ፡፡ እነዚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናታቸውም በኩል እንዲሁ በዝምድና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ማቴዎስ የተባለው ደገኛ ክርስቲያን የሸዋ ገዥ የነበረ ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ መድኃኒነ እግዚእንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፡፡ ሶስቱ ሴቶች ልጆችም እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ ሦስቱ እኅትማማቾችም ደጋጎቹን አባቶቻችንን ወለዱልን፡፡ እምነ ጽዮን የእነ ዜና ማርቆስን እናት ማርያም ዘመዳንና ወለደች፡፡ ትቤ ጽዮንም ሕፃን ሞዐን ወለደች፡፡ ክርስቶስ ዘመዳ ደግሞ ታላቁን አኖሬዎስን ወለደች፡፡ የፈጠጋሩ ገዥ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ የተክለ ሃይማኖትን እናት እግዚእ ኀረያን ወይም በሌላ ስሟ ሣራን ወለደ፡፡

Thursday, January 29, 2026

ጥር 21 ቀን የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት

በየዓመቱ ጥር 21 ቀን የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በመላው ዓለም ክርስትናን የተቀብሉ ብዙ ሀገራት አሉ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን እውነተኛ ታሪክ እንዲታይ አድርጎ ማክበር ከጥቂቶቹ በስተቀር ጎልቶ አይታይም። ይህም ማለት በዓሉን አያከብሩም ማለት ሳይሆን የበዓሉን ምስጢር ተርጉሞ ለሰዎች በሚረዳ መልኩ ማክበር እንደ ኢትዮጵያ (ኤርትራ) ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያለ ማንም የለም። ምሥጢሩ ለገባው ሰው በጆሮ የሰሙትን በዓይን ማየት እንዲሁም መኖር መቻል መታደል በመሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆች ሁልጊዜ በደስታ በዓሉን እናከብራለን። እንደቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ “ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ ተሸጋግራለች፡፡

ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” (ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል) ብሎ እንደተናገረው በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
... የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁミ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅስስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ባባ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ ቦሃላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡

Monday, January 26, 2026

ባህልና ሃይማኖት

ሃይመነ አሳመነ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን   “ማመን፣ መታመን፣ እምነት፣ ጽኑ ተስፋ፣ በልብ በረቂቅ ሐሳብ የሚሣል ማለት ነው፡፡   ትርጉሙም በአንድ አምላክ ማመን እና ለአንድ አምላክ መታመን ማለትን ያመለክታል ፤ በዓይናችን ለምናየው ለግዙፉ ዓለምና ለማይታየው ለረቂቁ ዓለም ፈጣሪ አስገኝ ፣ መጋቢ አለው ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመን ማለት ነው ።(አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፫፻፷፱) ይህ የሁሉ ፈጣሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው! ታዲያ ሁሉን ያስገኘ (የፈጠረ) እግዚአብሔር መሆኑን ያወቅነው በሃይማኖት ነው፤ በእምነት ነው፤ በኋላም “መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል” ብለን ጽኑ ተስፋ እናደርጋለን፡። ሃይማኖት የሚፈጸም፣ የሚሆን፣ በዓይን የማይታይ፣ በሥራ የሚገለጥ ረቂቅ የሆነ ነው፡፡



ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ረቂቅ የሆነ (በዓይን የማይታይ) መንገድ ነው፤ መንገድ ሩቅ እና ሩቅ ያሉትን ሰዎች እንደሚያገኛኝ ሃይማኖትም የፍጥረታት ፈጣሪ እግዚአብሔርን እና እኛን ሰዎችን ስለምታገናኘን በመንገድ ተመሰለች፡፡

ስለ ሃይማኖት በጥቂቱ ገለጽን እንጂ ሃይማኖት ብዙ ምሥጢር እና ትርጉም ያላት ናት! እምነትን (ሃይማኖትን) ከምግባር ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፤ እምነትና ሥነ ምግባር አብረው ሲሆኑ ነው እምነታችን ጽኑ ሆኖ ኃይልና ብርታት የሚሆነን፤ ስለዚህ ሃይማኖታችንን በሥራ ሊገለጥ ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ ‹‹..ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ…›› በማለት እንደ መከራቸው እምነታችን በሥራ የተገለጠ ፍሬን የሚያፈራ፣ ጨለማ ከተባለ ክፉ ምግባር መለየት እንዳለበት አስተምሮናል፡፡ (ኤፌ.፭፥፲፩)

እንዲሁም  ባሕል ማለት የአንድ ኅብረተሰብ አኗኗር ነው። እንደ የሰው ልጅ ጥናት «ባህል» የኅብረተሠቡ ቋንቋ ፣ ሥነ ጥበብ ፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሙዚቃ ፣ ጭፈራ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ አበሳሰል ፣ አለባበስ፣ ስነ ሕንጻ ፣ ሕግ ፣ አስተያየት፣ ፍልስፍና ፣ አፈ ታሪክ እና ብዙ ሌሎች ረገዶች ያጠቅልላል።