እንኳን ለፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ስባረ አጽም የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ
አበ ኩልነ አባ ተክለሃይማኖት አስተጋብአነ ለሥብሃተ እግዚአብሔር ( የሁላችን አባት አባ ተክለሃይማኖት እኛ ልጆችህን ዘወትር እግዚአብሔርን ለማመስገን የተጋን፣የነቃን፣ የበቃን አድርገን) ብሎ እንደተናገረው ዛሬ ምድረ ኢትዮጵያ ጻድቁ አባታችን በወንጌል ያረሰረሷት በፈተና ላይ ነችና ከጥፋት እንዲታደጓት ፈቃዳቸው ይሁንልን።
የኢቲሳ አንበሳ ተክልዬ ተነሳ
ወገንክን ታደገው ከኃጢአት አበሳ. . .
እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ የመረጣቸው ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን 1197 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ማለትም ‹‹አንዱ አብ ቅዱስ ነው አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ አመስግነውታል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ይኸውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ የወላጆቻቸው የቀድሞ ስማቸው ዘርዐ ዮሐንስና ሣራ ይባል ነበር፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል የትውልዳቸው መሠረት ኢያሱ ለሌዋውያን ክፍል ትሆን ዘንድ ከለያት ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ ስማቸው የተጠቀሰው እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን የወንድማማቾች ልጆች ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ 61ኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ይኸውም እንዴት ነው ቢሉ ትውልዱ ከአዳም ጀምሮ በካህኑ አሮን በኩል የሆነውና የሌዋዊያን ሊቀ ካህን የነበረው የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከታቦተ ጽዮንና ከብዙ ሌዋዊያን ካህናት ጋር ሊቀ ካህን ሆኖ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አክሱም ተቀምጦ ኖረ፡፡ የኦሪትንም ሕግ እየዞረ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ ትውልዱም በአብርሃ ወአጽብሓና በአባ ሰላማ ዘመን እስከነበረው እንበረም የሚባለው ጻድቅ ድረስ ደረሰ፡፡ የእንበረምም ትውልድ ደገኛው ሕይወት ብነ በጽዮን ድረስ ደረሰ፡፡ ሕይወት ብነ በጽዮንም የደማስቆ ምድር ከሚሏት ከወለቃ ሀገር የመኮንን ልጅ የሆነችውን ወለተ ሳውልን አግብቶ አበይድላን ወለደ፡፡ አበ ይድላም በንጉሡ ድልዓዥን ዘመነ መንግሥት ለ150 ካህናት አለቃ ሆኖ በወለቃ ሀገር የክርስቶስን የወንጌል ሕግ እያስተማረ ብዙዎችን አጠመቀ፡፡ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ እያስተማረ መጥቶ በሸዋ ምድር ተቀመጠ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳነጸ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትንም ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹በሸዋ ጽላልሽ ተቀምጦ ሲያስተምርም በአንዲት ቀን እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ያጠምቅ ነበር›› በማለት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይመሰክርለታል፡፡

አበይድላ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር ከሸዋ ጽላልሽ ምድረ ዞረሬ ሚስት አግቶ ሀበነ እግዚእን ወለደ፤ ሀበነ እግዚእም በኩረ ጽዮንን ወለደ፤ በኩረ ጽዮንም ሕዝበ ቀድስን ወለደ፤ እርሱም ነገደ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ሕዝበ ቀድስም ብርሃነ መስቀልን ወለደ፤ እርሱም ዐቃቢነ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀልም ሕይወት ብነን ወለደ፤ እርሱም ሴትን ወለደ፡፡ ሴትም ወረደ ምሕረትን ወለደ፡፡ ወረደ ምሕረትም ዘካርያስን ወለደ፡፡ ዘካርያስም የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የሆኑ 6 ወንድማማች ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም እንድርያስ፣ አርከሌድስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብ፣ ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ዮናስ ናቸው፡፡ እንድርያስም ሳሙኤል ዘወገግን ወለደ፤ አርከሌድስም ሕፃን ሞዐን ወለደ፤ ዘርዐ አብርሃምም ታላቁን አኖርዮስን ወለደ፤ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብም ተክለ ሃይማኖትን ወለደ፤ ቀሲስ ዮሐንስም ዜና ማርቆስን ወለደ፣ ቀሲስ ዮናስ ደግሞ የፈጠጋሩን ማትያስንና ገላውዲዮስን ወለዳቸው፡፡ ገላውዲዮስም የመሐግሉ ቀውስጦስን ወለደ፡፡ እነዚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናታቸውም በኩል እንዲሁ በዝምድና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ማቴዎስ የተባለው ደገኛ ክርስቲያን የሸዋ ገዥ የነበረ ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ መድኃኒነ እግዚእንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፡፡ ሶስቱ ሴቶች ልጆችም እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ ሦስቱ እኅትማማቾችም ደጋጎቹን አባቶቻችንን ወለዱልን፡፡ እምነ ጽዮን የእነ ዜና ማርቆስን እናት ማርያም ዘመዳንና ወለደች፡፡ ትቤ ጽዮንም ሕፃን ሞዐን ወለደች፡፡ ክርስቶስ ዘመዳ ደግሞ ታላቁን አኖሬዎስን ወለደች፡፡ የፈጠጋሩ ገዥ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ የተክለ ሃይማኖትን እናት እግዚእ ኀረያን ወይም በሌላ ስሟ ሣራን ወለደ፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከልጅነታቸው ጀምሮ በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በ15 እና በ22 ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ (ጌርሎስ) ዲቁናንና ቅስናን ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ያገለግሉ እንደነበር በዚህ ይታወቀል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን አባታችን ከጓደኞቻቸው ጋር ለአደን ወደ ዱር ሄደው ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ታያቸው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ‹‹እንደዚህ ባለ ገናንነት የማይህ ጌታዬ ማነህ?›› ባሉት ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ዘወትር የምጠብቅህ ካንተ የማልለይ እናትህንና አባትህንም ስላንተ ከውኃ ስጥመትና ከምርኮ ያዳንኳቸው እኔ ሚካኤል ነኝ፡፡ ከእንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሁን፤ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ሰውን በትምህርት የምታድን ሁን እንጂ፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ጽኑዕ ሥልጣን ሰጥቶሃልና፤ ሙት ታስነሣለህ፤ ድውያንን ትፈውሳለህ፤ አጋንንትም አንተን በመፍራት ይሸሻሉ፡፡ ስምህ ፍሥሐ ጽዮን አይሁን፤ ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፡፡ ትርጓሜውም ተክለ አብ፥ ተክለ ወልድ፥ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው›› አላቸው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ይህን ሲነግራቸው ጌታችን በሥጋ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበር ሆኖ መልከ መልካም ጎልማሳ መስሎ ታያቸው፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ እንዴት ሰነበትክ? ቸር አለህን?›› አላቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ጌታዬ ሆይ አንተ ማነህ?›› ብለው ሲጠይቁት ጌታችንም ‹‹እኔ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ነኝ፤ በናትህ ማኅፀን ፈጥሬህ ያከበርኩህ እኔ ነኝ፡፡ በተወለድክ በሦስተኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለህ ታመሰግነኝ ዘንድ የምስጋና ሀብት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ በርሃብ ዘመን በቤት የሚያሻው ምግብ ሁሉ ቅቤው፣ የስንዴው ዱቄት በእናት በአባትህ ቤት ይመላ ዘንድ በእጅህ ሀብተ በረከት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ ያንን ሰው አንተን በተጣላ ጊዜ በነፋስ አውታር የሰቀለኩት በመዓት ጨንገር የገረፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ውኃ ጠምቶህ በለመንከኝ ጊዜ ከደረቅ መሬት የጣፈጠ ውኃ ያመነጨሁልህ እኔ ነኝ፡፡ ከልጅነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ተአምራት እያደረግሁ በአንተ እጅ የታመሙትን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ወደፊትም
አደርግልሃለሁ›› አላቸው፡፡ ይህንን ብሎ በእጆቹ ባረካቸውና ‹‹ንሣእ መንፈስ ቅዱስ›› ብሎ የሹመትን ሀብት አሳደረባቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሁን፤ በምድርም የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሁን፤ አንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው፤ የላከኝ አባቴንም መስማቱ ነው፡፡ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ ማለቱ ነው፡፡ የላከኝ አባቴንም እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ቀድሞ ለሐዋርያት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ከሐዋርያትም ሹመትን የተቀበለ ጳጳሱ ትሾምና ትሽር፣ ትተክልና ትነቅል ዘንድ ሥልጣንን ሰጠህ፡፡ ይህንንም ያደረኩልህ የጳጳሱን ቃል በመናቅ አይደለም፡፡ የፍቅሬን ጽናት ባንተ እገልጽ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ሐዋርያት ወዳልደረሱበት ሕዝብ በመምህርነት እልክህ ዘንድ በሚካኤል ቃል አዲስ ስም አወጣሁልህ፡፡ አንተም በማናቸውም ሥራ ከእነርሱ አታንስም፣ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁና፡፡ ሰውን ሁሉ በእኔ ስም እያስተማርክ ታሳምን ዘንድ፣ ሚካኤልም ባሰብከው ሥራ ሁሉ ረዳት ይሁንህ፣ ሁል ጊዜ ካንተ አይለይም፤ በምትሄድበትም ጎዳና ሁሉ እርሱ መሪ ይሁንህ፤ እኔም ባለ ዘመንህ ሁሉ አልለይህም›› ካላቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ዐረገ፡፡
ብፁዕ አባታችንም እጅ ነሥተው ‹‹ለእኔ ለኀጥኡ የማይገባኝ ሲሆን ይህን ሁሉ ጸጋ የጠኸኝ ስምህ በሰማይ በምድር የተመሰገነ ይሁን›› አሉ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሀብተ ኃይልን የተመሉ ሆኑ፡፡ ወደቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ሀብት ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥተው ጨረሱ፡፡ ከዚያም ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ›› ብለው ቤታቸውን እንደተከፈተ ትተው ወንጌልን ለማስተማር ወጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት ስለመለሱት በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ተብለዋል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹ፍሥሐ ጽዮን› ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሕፃኑ ፍሥሐ ጽዮን ወደ ጫካ ለአደን ሔዱ፡፡ በዚያች ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡ፤ አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባል፤ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አበሠራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ገዳም (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፻፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም (የዐፅም ስባሪ) አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ዅሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡
ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን ተቃረበ፡፡ በዚህ ጊዜ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነገራቸው፡፡ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደ ተጠቀሰው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይና በኢየሩሳሌም ገዳማት ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡
በአጠቃላይ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› (ማቴ. ፲፥፵-፵፪) በማለት ጌታችን የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን የፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የልደታቸውን፤ ጥር ፬ ቀን የስባረ ዐፅማቸውን (እግራቸው የተሰበረበትን)፤ ግንቦት ፲፪ ቀን የፍልሰተ ዐፅማቸውን፤ ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፤ የጻድቁ በረከት አይለየን፡፡
No comments:
Post a Comment