፠ ሰባት ራሶች፦ የተባሉት በመጨረሻው በሐሳዊ መሲህ ዘመን የሚፈጸሙ ሰባቱ ዋና ዋና ኃጢያቶች ናቸው። እነዚህም 7ቱ አርዕስተ ኃጣውዕ ወይም 7ቱ የኃጢአት ራሶች ይባላሉ!
Wednesday, February 25, 2026
ሰባቱ የኃጢአት ራሶች
Sunday, February 1, 2026
ጾመ ነነዌ
ጾመ ነነዌ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዷ ስትኾን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ይህቺ ጾም የምትጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሟ የምትጀመርበት ቀን ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡ ቀኑ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፋ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ቀን ይረዝማል፡፡ ጾመ ነነዌ በእነዚህ ፴፭ ቀናት ውስጥ ስትመላለስ (ከፍ እና ዝቅ ስትል) ትኖራለች፤ ከተጠቀሱት ዕለታት አትወርድም፤ አትወጣም፡፡ በዚህ ዓመትም (፳፻፲፰ዓ.ም) ጥር ፳፭ ቀን ትጀመራለች፡፡
‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሚለው የጽሑፋችን ርእስ እንደሚያስረዳው ይህቺን የሦስት ቀን ጾም የጾሟት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው /ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪/፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የኾነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶባት ነበር /ዮናስ ፬፥፲፩/፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኀጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው /ሉቃ.፲፩፥፴/፡፡
ዮናስ የስሙ ትርጕም ‹ርግብ› ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናግሯል /፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩/፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል /፩ኛነገ.፲፯፥፲፱/፡፡ መድኀኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ኾድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል /ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪/፡፡
ተክለሃይማኖት ፀሐይ
እንኳን ለፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ስባረ አጽም የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ
አበ ኩልነ አባ ተክለሃይማኖት አስተጋብአነ ለሥብሃተ እግዚአብሔር ( የሁላችን አባት አባ ተክለሃይማኖት እኛ ልጆችህን ዘወትር እግዚአብሔርን ለማመስገን የተጋን፣የነቃን፣ የበቃን አድርገን) ብሎ እንደተናገረው ዛሬ ምድረ ኢትዮጵያ ጻድቁ አባታችን በወንጌል ያረሰረሷት በፈተና ላይ ነችና ከጥፋት እንዲታደጓት ፈቃዳቸው ይሁንልን።
ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል የትውልዳቸው መሠረት ኢያሱ ለሌዋውያን ክፍል ትሆን ዘንድ ከለያት ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ ስማቸው የተጠቀሰው እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን የወንድማማቾች ልጆች ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ 61ኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ይኸውም እንዴት ነው ቢሉ ትውልዱ ከአዳም ጀምሮ በካህኑ አሮን በኩል የሆነውና የሌዋዊያን ሊቀ ካህን የነበረው የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከታቦተ ጽዮንና ከብዙ ሌዋዊያን ካህናት ጋር ሊቀ ካህን ሆኖ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አክሱም ተቀምጦ ኖረ፡፡ የኦሪትንም ሕግ እየዞረ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ ትውልዱም በአብርሃ ወአጽብሓና በአባ ሰላማ ዘመን እስከነበረው እንበረም የሚባለው ጻድቅ ድረስ ደረሰ፡፡ የእንበረምም ትውልድ ደገኛው ሕይወት ብነ በጽዮን ድረስ ደረሰ፡፡ ሕይወት ብነ በጽዮንም የደማስቆ ምድር ከሚሏት ከወለቃ ሀገር የመኮንን ልጅ የሆነችውን ወለተ ሳውልን አግብቶ አበይድላን ወለደ፡፡ አበ ይድላም በንጉሡ ድልዓዥን ዘመነ መንግሥት ለ150 ካህናት አለቃ ሆኖ በወለቃ ሀገር የክርስቶስን የወንጌል ሕግ እያስተማረ ብዙዎችን አጠመቀ፡፡ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ እያስተማረ መጥቶ በሸዋ ምድር ተቀመጠ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳነጸ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትንም ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹በሸዋ ጽላልሽ ተቀምጦ ሲያስተምርም በአንዲት ቀን እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ያጠምቅ ነበር›› በማለት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይመሰክርለታል፡፡


