Monday, December 29, 2025

ጾመ ጋድ (ገሃድ)

በቅድሚያ እንኳን ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ የዘንድሮው ዓመት 2018 ዘመነ ማርቆስ የገና እና የጥምቀት በዓላት እረቡዕ እና ሰኞ በመዋላቸው በምእመናን የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች በሊቃውንት ጉባኤ የሚመለሱ ቢሆንም ቤተክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት በመሆኗ አባቶቻችን አስቀድመው ሥርዓት ሠርተውልናል። በመሆኑም በመጠኑ ስለዘንድሮው ዓመት የገናና የጥምቀት በዓል ጋድ ወይም ገሃድ ጾም በመጠኑ ሃሳብ ለማካፈል ወደድኩ። ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ? በፍትሃ ነገሥት /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/ የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ ተብሎ በተጻፈው መሰረትገናና ጥምቀት እረቡዕና ዓርብ ላይ ቢውሉ መብላት ይቻላል ማለት ነው ስለዚህ የ2018 ዓ/ም ገና ረቡዕ ቢውልም በዓለ ልደቱ የሚከበርበት እለት በመሆኑ ክርስቲያኖች በሥርአተ ቤተክርስቲያን በታዘዘው መሰረት ከቤተክርስቲያን አገልግሎት መልስ በቤታቸው በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ተፈቅዷል። ጋድ ገሃድ ፍትሐ ነገሥት፡ የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 566/ ትንታኔ፡ የገና ጾም 44 ቀናትን ይይዛል፡፡ 40 ጾመ ነቢያት 3 ጾመ አብርሃም ሶርያዊ 1 ጋድ ድምር 44
የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 565/ ነገር ግን አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡ ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን? መልስ፡ በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 15፣ ቁ 565 እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ስለ ገና ጾም ሲገልጥ «መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው» ይላል /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 568/፡፡ ይህም ከገና ጾም ተሸርፎ የሚጾም ነገር እንደሌለው ያሳያል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ጋድ(ገሃድ) ነው፡፡ ገሃድ ማለት ለውጥ(ምትክ) ወይም ልዋጭ፤ እንዲሁም ግልጥ፣ ተገላጭ በማለት ይተረጎማል፡፡ ይህንንም ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ጋድ(ገሃድ) እንዲህ ይተረጉሙታል፡- “ገና፣ የጥምቀት ከተራ (የልደትና የጥምቀት ዋዜማ) እንደ ዐርብ ረቡዕ እና ፍልሰታ፣ እንደ ሑዳዴ የሚጾም፡፡ ትርጓሜው የሚገለጥ፣ ተገላጭ፣ ግልጥ ማለት ነው፡፡ ጌታችን እንደ ሰውነቱ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ መታየቱን ያስረዳል” (ደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ ፪፻፴፪)፡፡ ጥር ፲ የሚነበበው ስንክሳር በጥምቀት ዋዜማ መጾም እንደሚገባ ሲገልጽ፡- “በዚች ዕለት ምንም መብልን ሳይቀምሱ ምእመናን ሁሉ እስከ ምሽት ይጾሙ ዘንድ ከእኛ አስቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓትን ሠሩ፤ በምሽትም ቢሆን በታላቁ ጾም ከሚበላው በቀር ጥሉላትን አይቅመሱ፡፡ በዚህች ዕለት ምእመናን እስከ ምሽት እንዲጾሙት ያዘዙበት ምክንያት ይህ ነው፡- የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዐርብ ቀን ቢውል በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲያከብሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል፡፡ እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓሎቹ ናቸውና፡፡” ይህም ማለት ልደት እና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ከዋሉ በዋዜማው ማክሰኞና ሐሙስ ይጾማሉ። ረቡዕና ዐርብ ምንም እንኳን የጾም ቀናት ቢሆኑም የፍስክ ቀን ሆነው ይከበራሉ። የልደት እና የጥምቀት በዓል እሑድ ቢውሉ በዋዜማው ቅዳሜ የጥሉላት ምግብ አይበላም። እንዲሁም ልደት እና ጥምቀት ሰኞ ቢውሉ እሑድ ጥሉላት አይበላም። እንደ ሌሎች የአጽማዋት ቀናት እህልና ውኃ ግን አይጾሙም። ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ሲገልጽ፡- “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፤ በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውንም ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍሱም ትታዘዝ ዘንድ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ መጾም እንደሚገባም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታለች፡፡ (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፬)

Friday, December 19, 2025

የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?'' መዝ 137፥1

ሕዝበ እሥራኤል የፈጣሪያቸውን ህግና ሥርዓት መጠበቅ እየተሳናቸው ብዙ ጊዜ በስደትና በጦርነት ተቀጥተዋል። ይሁን እንጅ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ለአባቶቻቸው የገባው ቃል ኪዳን ስላለ የጠፉ ቢመስሉም እንደገና ያበረታቸዋል። 

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የአባቶቹን ሃዘንና ሰቆቃ በምርኮ ሳሉ የደረሰባቸውንና ያደረጉትን አስታውሶ የተናገረውን ነው መነሻ ያደረኩት ''በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?'' መዝ 137፥1

ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ምክንያት ልጆቿ ስደትን እንደ ትልቅ እድል በመቁጠር በሰው ሀገር መኖርን ተለማምደዋል። ብዙዎች በገዛ ሀገራቸው የስደተኛነት ስሜት እየተሰማቸው የሰው ሀገር ይናፍቃሉ። ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በመኪና ተጉዞ ቤተሰብ ማግኘት የማይታሰብ እየሆነ ነው። አዲስ አበባ ተውባለች ደምቃለች የሀገሪቱ ሰፊው ገጠራማ ክፍል ግን በሰላም እጦት ጭንቀት ላይ ይገኛል። ጦርነት፣ ርኃብ፣ ስደት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ ነገር የሚነገር ዜና አይደለም። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው ተበደልኩ ብሎ ሲናገር ወይም አንዱ ስለሌላው መበደል ሃሳብ ቢሰጥ እንደቁም ነገር መቁጠር ካቆምን ሰነባብተናል። ይህ ሁሉ ችግር እያለ በዚህ ሰቆቃ ለበዛበት ማህበረሰብ የማይሆኑ አጀንዳዎችን የሚፈጥሩ አንዳንድ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በውዳሴ ከንቱ ተጠልፈው ''በቁስሉ ላይ እሾህ ስደድበት'' በሚመስል መልኩ ህዝቡን ግራ ያጋቡታል። ቢቻል ስለሃገር ሰላምና አንድነት መሥራት ይገባ ነበር ካልሆነም ህዝቡ ካለበት ችግር የሚወጣበትን ምክርና በጎ ሃሳብ ማቅረብ ሲገባ መለያየትን የሚያመጣ የግል ሃሳብ ማምጣት ለህዝብ ዴንታ ቢስ መሆን አይደለምን?

እውነት ለእኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች በዚህ ሰዓት ጸሎት ነው መዝሙር ነው የሚያስፈልገው? ስሜትን ተወት አድርጎ በማስተዋል ነገሮችን ብናደርግ እግዚአብሔርም ይሰማናልና ቆም ብለን እናስብ። 

መዝሙር ማለት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የደስታ ጸሎት ወይም ምስጋና ማለት ነው ''ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር'' ያዕ 5፥13 እውነት እኛ ኢትዮጳያውያን በዚህ ወቅት ደስተኞች ነን?