ከአባቶቻችን የወረስነው አባባል ''የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል'' ይላል። እውነትም ወድቆ የተገኘ ነገር ሁሉ የፈቀደውን ያደርግበታል ስለዚህ ለማንም የሚጠቅመው ወድቆ አለመገኘት ነው።
ክፉ የሚባለው ጨካኝ፣ የማይራራ፣ እራስ ወዳድ ሃዘኔታ የሌለው ወዘተ ማለት ሲሆን መልካም ማለት ደግሞ ማዘን፣መራራት፣ ለሌላው ማሰብ፣ በኔ ሊደረግ የማይገባውን በሌላው አላደርግም ወዘተ ብሎ እራስን መግዛት ማለት ነው። አሸናፊነት ሁልጊዜ የበላይ መሆን ወይም ከሌላው በልጦ መገኘት ብቻ አይደለም። ክፉ ለሚያደርግ መልካም መመለስ አሸናፊነት ነው። የበደለን ይቅር ማለት አሸናፊነት ነው። የተቀሙትን መተው አሸናፊነት ነው ከዚህ አንጻር ብዙ ማለት ይቻላል።
ሰው መሸነፍ የሚጀምረው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባ እለት ነው። በተለይ ክርስቲያን በፍሱም ተስፋ መቁረጥ የለበትም። ቅዱስ ጳውሎስ ለእብራውያን በጻፈው መልእክቱ'' እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ'' እብ 12፥1 ብሎ እንደተናገረው ፈተና በማንኛውም መልኩ ቢገጥመን ልናሸንፈው እንደምንችል ከአባቶቻችን ተምረናል።
ክርስትና ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ የደም ዋጋ እየተከፈለበት ዛሬ ላይ የደረሰ ሃይማኖት ነው። ዛሬ በሰዎች ኃጢአት መብዛት የሃሳብ መለያየት በዝቶ ሁሉም የግል ሃሳቡን እያፈለቀ ብዙ ቤተ እምነት (Denomination) ቢፈጠርም መነሻው ግን አንድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ''በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ'' ኤፌ 4፥5 ብሎ እንደተናገረው የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር አንድ ነው። ወደ እርሱም የምንቀርብባት መንገድ አንዲት ናት እርስዋም አባቶቻችን የተጓዙባት ለነፍሳቸውም እረፍት ያገኙባት ናት። እርስዋ ቀዳማዊት ናት ደኃራዊት አይደለችም አዳም፣ አቤል፣ሴት፣ሄኖክ፣ኖህ፣አብርሃም፣ይስሃቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ዳዊት፣ነቢያት፣ሐዋርያት የተጓዙባት ቀጥተኛ መንገድ ናት። ''ግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ'' ኤር 6፥16
