ዛሬ ላይ ብዙዎች ኢትዮጵያን የመሰለች እናት እያላቸው ማንነት ፍለጋ የሚዋትቱት በገዛ ሀገራቸው እንደ ባይተዋር በመታየታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። "ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም" እንዲሉ ስላለፈው መጥፎ ነገር ጊዜ ማጥፋት ሞኝነት ነው። መፍትሄው። ያለፈውን በታሪክነቱ መማሪያ አድርጎ ለወደፊቱ ይህን ክፉ ተግባር የሚፈጽሙ ወገኖችን እድል በመንሳት ታግሎ እኩልነት ማምጣት ብቻ ነው ። አባቶቻችን "በሀገርና በእናት ቀልድ የለም" ይላሉ ታዲያ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ልጆች አድርጎን በሰዎች ምክንያት እንዴት በእናታችን እንደራደራለን?
በግልጽ መታወቅ ያለበት የግል ማንነትና የጋራ ማንነት የተለያዩ ናቸው። በኢትዮጵያ ምድር ለተገኘን ሁላችን ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን ነው። ይኽን ማንነት ደግሞ ሰዎች የሰጡን ማንነት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ያገኘነው ነው። ይኽን ማንነት በተልካሻ ምክንያት የሚጥል የተሸናፊዎች ሁሉ ተሸናፊ ነው። እናት አንድ ጊዜ ትወልዳለች ለሁልጊዜ እናት ትባላለች። የወለደች እናት እያለች በምንም መስፈርት ሌላዋ እናት ልትባል አትችልም።
ስለዚህ እኛ ዛሬ ከእናታችን ጉያ ለመውጣት የምንፈራገጥ ሁላችን ነገ ምንደኛ ሆነን ለመኖር እየታገልን እንደሆነ እናስብ። እኔ በግሌ ሁልጊዜ ጸሎቴ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ወንድሜም እህቴም እንደሆነ የማስብበት ህሊና ፈጣሪ አምላክ እግዚአብሔር እንዳይነሳኝ ነው። ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ያድለን።