Friday, February 3, 2017

የማልወደውን አደርጋለሁ !

 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ እንዳለ ዮሐ 8፥12 እርሱ ለመረጣቸው ሁሉን ትተው ለተከተሉት ኃዋርያትም እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ብሏቸዋል ማቴ 5፥14

ዓለም በኃጢዓት ጨለማ ውስጥ ተውጦ ሳለ እውነተኛው ብርሃን መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለአዳም የገባውን ቃል በፈጸመ ጊዜ ጨለማው ዓለም ብርሃን ወጥቶለታል። ይህም ሆኖ የሰው ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመምጣት ሲቸገሩ ታይተዋል። በዚህም ምክንያት። የብርሃኑን መንገድ የሚያሳዩ ኃዋርያትን መርጦ ወደ ዓለም ልኳቸዋል። ማር 16፥15 ዮሐ 17፥18



በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ወቅት ነበር ቅ/ጳውሎስ ለሐዋርያነት የተጠራው።  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት አንደበት ብርሃነ ዓለም ይባላል። የዓለም ብርሃን ማለት ነው።  በቤተክርስቲያናችን ዘወትር ከሚነበቡት መጻሕፍት መካከል የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ይጘኙበታል። በመልክቱ አብዛኛውን ጊዜ የገለጸው በቀድሞ ህይዎቱ አሳዳጅ ስለመሆኑ እና ከዚህ ህይዎት እንዴት እንደተጠራ ሲሆን በተለይ እራሱን እየወቀሰ የጻፋቸው መልእክታቱ ልብን ይነካሉ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም።የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ።በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም።የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ።በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ። ሮሜ 7፥15

የእግዚአብሔር ምርጥ እቃ የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ካለ እኛማ ምንኛ በደለኞች ነን! የእግዚአብሔር ምህረት ምን ያክል የበዛ ነው! ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ (ሰቆቃው ኤርምያስ ምዕ. 3፥22)
ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። 
ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። እንዳለው በኃጢአትና በበደላችን ብዛት እንዳንጠፋ የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ አማላጅነት አይለየን።

No comments:

Post a Comment