Saturday, December 29, 2012

የጸናውን አስቡ እብ 12፥3

 
ሰሞኑን በምንሰማው ነገር ብዙዎቻችን ክርስቲያኖች በተለያየ ሃሳብ ውስጥ እንዳለን ይታወቃል። በተለይ የወሬ ገበያው የደራላቸው ሚዲያዎች የቤተክርስቲያንን ጉዳይ የራሳቸው በማስመሰል ብዙዎችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። የቤተክርስቲያን ጉዳይ እለት እለት የሚያስጨንቃቸው አካላት እንዳሉት ሁሉ አንድነቷና ሰላሟ ወደነበረበት ቢመለስ የእለት እንጀራቸው የሚያሳስባቸው ጥቂቶች አይደሉም። ምክንያቱም በአባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ለወንበዴዎች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው ነበር። “ ግር ግር ለሌባ ይመቻል አይደል ” የሚባለው ፣ አሁን ስለ ሰላም ከሚጨነቁት አካላት በላይ የነበረው አለመግባባት እንዲቀጥል የሚደክሙት ወገኞች ስራ በዝቶባቸዋል። በጣም የሚደንቀው በሰላም እና በአንድነት እየኖሩ ሁሉን ማግኘት እየተቻለ ለምን ቤተክርስቲያኒቱን በጥብጠው እራሳቸውን እንደሚበጠብጡ ነው የማይገባኝ፥ የሰላም ሰው የፍቅር ሰው መባል በሰውም ሆነ በእግዚአብሔርም ዘንድ ያስከብራል እንጅ ውርደት የለበትም።
ዛሬ ላይ በጎ የሆነው ነገር እንደውርደት እየተቆጠረ ነው፥ ሰርቶ ማግኘት እየተቻለ ሰርቆ መብላት አስደሳች ከሆነ ምን ማለት ይቻላል፥ እባካችሁ የዚህ ጉዳይ ባለቤቶች ለቆማችሁባት ቤተክርስቲያን እዘኑላት፥ ጫንቃዋ እየደማ ነው፣ ለነገ የማይሽር ጠባሳ እያስቀመጣችሁ ነው። አክብራ ያስከበረቻችሁን ቤተክርስቲያን መሳለቂያ አታድርጓት፣ የገባችሁትን ቃል አስቡ ፣ የተጻፈውንም በቃል መናገር ብጫ ሳይሆን በተግባር ለማሳየት ሞክሩ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። የሐ ሥ 20፥28 ”  “ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ። 1ኛ ጴጥ 5፥3 ” ያለንበት ዘመን እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የቤተክርስቲያን አባቶች ብዙ ፈተና እንደሚኖርባቸው እናምናለን። ነገር ግን ፈተናውን በጽናት ሲያልፉ ማየት እንጅ ሲሸነፍ ማየት ለህዝባችን ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ያስከትላል።
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደነገሩን ከሰው በጎ ነገር የሚጠፋበት ዘመን እንደሚመጣ እንረዳለን። “ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል።,እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል አሁን ይሸበራሉ። ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ። ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና።” ትን, ሚክ 7፥2
የብዙ ኦርቶዶክሳውያን ህልም የቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ታዲያ ይህንን ሰላምና አንድነት እንዴት እናምጣው? እውነት ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያለው ችግር መፍትሄ የለሽ ነው? አይመስለኝም እውነት እኛ እርቅ ፈላጊዎች ከሆንን በጣም ቀላል ነው። እስቲ መጀመሪያ እኛ እራሳችን ከራሳችን ጋር እንታረቅ? እስቲ ከእግዚአብሔር ጋር እንታረቅ? ለማስታረቅ ተፈተፍ የምንለው አካላት አስቀድመን በያለንበት ስለእርቅ እንስበክ? ትልቁ ችግር እኮ እኛ ለማስታረቅ እንጅ የመታረቅ ግዴታ እንዳለብን አለማመናችን ነው። ታዲያ ከራሱና ከሌላው ጋር ያልታረቀ እንዴት ሊያስታርቅ ይችላል? ያልቆረበ ከመቼ ወዲህ ነው አቁራቢ የሚሆነው? ችግሩ እዚህ ላይ ነው  ለመታረቅም ሆነ ለማስታረቅ ክርስቶስን መምሰል ያስፈልጋል። እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ 1ኛ ቆሮ 11፥1 ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮ 5፥18
አሁን የሚታየው ነገር የተገለበጠ ይመስለኛል የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ውጭ ነው ያሉት። በሃገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በዚህ በውጭው ዓለም ትላንት ቤተክርስቲያን አንቱ ብላ አክብራ ያስከበረቻቸው አባቶች እንዲሁም ለብዙ ዘመናት በአብነት ትምህርት ቤቶች ቃለእግዚአብሔር ለመቅሰም እድሜያቸውን የጨረሱ ምሁራን መጠጊያ አጥተው ችግር ላይ ወድቀዋል። በተቃራኒው ምንም የማይገዳቸው ቤተክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው እነርሱም የማያውቋት በውስጥ ተሰግስገዋል ። ይህን እያደረጉ ያሉት ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የተባሉት ናቸው። ዛሬ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ወንዝና ድንበር መመዘኛ ሆነዋል ። ምናልባት ድፍረት ባይሆንብኝ ስርዓተ ቤተክርስቲያንን ባልጠበቀ መልኩ ለብዙዎች የአገልግሎት ፈቃድ ተሰጥቷል። ይህ የሚያሳየው ለመንጋው የማይራሩ እንደተባለው ለህዝቡ አለማሰብ ነው። ለዚያም ይመስለኛል የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ቅን ፍርድን ለመፍረድ ባለመቻላቸው በልጆችና በአላዋቂዎች እጅ የወደቁት።   
ቀደም ሲል የነበሩት አባቶች ሲሰነዝሩት የነበረውን ሃሳብ አንዳንዶቻችን በሞኝነት እንመለከተው ነበር። “ የጨው ክምር ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል ” እንደሚባለው ማለት ነው። ዛሬ ላይ የተናገሩት ነገር እውን ሆኖ ስናየው እውነትም እጅግ ሞኞችና አርቆ አስተዋዮች አለመሆናችንን እንገነዘባለን።
እውነተኞቹ አባቶች በጳጳሳት ሹመት እንዲሁም በሌሎች የክህነት አሰጣጥ ስርዓትና መመዘኛ ዙሪያ ሳይናገሩ አያልፉም ነበር። ነገር ግን ማን ሰምቶ እንዲህ በስራ ተገልጦ ካላየን መች እናምናለን። ቤተክርስቲያናችንን አክብረን የማስከበር ኃላፊነት ሁላችንም ኦርቶዶክሳውያን ግዴታ አለብን ። በያለንበት ስለቤተክርስቲያናችን ስርዓት እንቆርቆር። ቤተክርስቲያናችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ተጠያቂዎቹ አባቶች ብቻ አይደሉም። ብዙዎቻችን ከአባቶቻችን በረከት ለማግኘት በመሽቀዳደም ፈንታ ድንጋይ ስንወረውር የነበርን ነን።  ልዩ ዓይነት በሆነ እንግዳ ወሬ አንረበሽ። ቤተክርስቲያንን የሚመራት ክርስቶስ እንደሆነ እንመን። ዛሬ የቤተክርስቲያኒቱን ጉዳይ ቸል በማለት ለራሳቸው ጥቅም የሚሮጡትን አንመልከት። የጸናውን አስቡ << ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ኢሳ 28፥16 በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። እብ 12፥3  እንደተባለ አጽማቸውን ከስክሰው እስከዛሬ ያቆዩልንን አባቶቻችንን እየተመለከትን በጽናት እንቁም << የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። እብ 13፥7
 
አንድ  ነገር አለ ምናልባት የሰይጣንን መንገድ በቅጡ ያልተረዱ ክርስቲያኖች የራሳቸውን የቤት ስራ ትተው ስለአባቶችና ስለሌሎች ሲያወሩና ሲጽፉ መልካም ያደረጉ እየመሰላቸው እንዳይዘናጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ ። ሁሉን እንደስራው ለሚከፍለው አምላክ ፍርዱን እንዲሰጥ በጸሎት መጠየቅ እንጅ እኛው ፈራጆች ከሆንን ይፈረድብናል << እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ማቴ 7፥1 እርሱ ለእያንዳንዱ እንደስራው ያስረክበዋል ሮሜ 2፥6
ብዙዎቻችን  የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ አያገባንም ብለን ከመሳለምና ከማስቀደስ ያለፈ ተሳትፎ ሳናደርግ በመቆየታችን ብዙው ነገር እንግዳ ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን ከቀድሞ ጀምሮ በየዘመናቱ ቤተክርስቲያን አምጣ ባልወለደቻቸው ልጆች ስትፈተን ነው የኖረችው። ይህ ወደፊትም ይቀጥላል ,, እስከመጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል ብሎ ጌታ እንደተናገረው በዚህ ፈተና ውስጥ ለማለፍ ጽናት ይጠይቃል። የጳጳሱ የመነኩሴው፣ የቄሱ የዲያቆኑ፣ የዘማሪው የሰባኪው ድክመት ከእምነታችን ሊያናውጸን አይገባም ይልቁንም በዚህ ወቅት ነው እራሳችንን መፈተን ያለብን። እኔ ማነኝ ያባቴስ ቤት ምንድነው 1ኛ ሳሙ 18፥18  እንዳለው ሰው እራሳችንን ዝቅ አድርገን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይጠበቅብናል።
 
በተለያየ መንገድ ስሜታችንን ለመግለጽ የምንሞክረውም ቢሆን የምናፈልቀውን ሃሳብ ደጋግመን መፈተሽ እንደሚኖርብን ባንዘነጋው መልካም ነው ።ያለንበት ዘመን እራስንም የማያምኑበት ስለሆነ በሃሳባችን መደገፍ አይገባም።  “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” ምሳ 3፥5 እንዳለው ጠቢቡ እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል ነው ማለትን ብናቆም የተሻለ ነው። የሰላም አምላክ ለቤተክርስቲያናችን ሰላምን ያምጣልን።                                              
                                           

 

No comments:

Post a Comment