Saturday, December 31, 2011

ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም። ሚክ 2፥3

ዛሬ ስላለንበት ዘመን ስንናገር ምናልባትም ማንም የማይቀማንን ሙሉ መብት ተጠቅመን  በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። ምክንያቱም  ክፉም ይሁን በጎ ዘመኑ እኛ የተፈጠርንበት በመሆኑ የኛ ዘመን ነው ብሎ ለመናገር ፈቃድ አያስፈልገውም። አንድን ነገር የኔ ነው ለማለት በህግ ፊት የሚቀርብ የባለቤትነት ማስረጃ ያስፈልጋል።እናም የኛ ማስረጃ በዚህ ዘመን መፈጠራችን ብቻ ነው።

Thursday, December 29, 2011

እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሉቃ 1፥19


ዛሬ በሃገራችን በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል የሚታሰብበት እለት ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል በዛሬው እለት ሠለስቱ ደቂቅን ( ሶስቱን ወጣቶች ) ከእሳት ያወጣበት እለት ነው። የቤተክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት ዓመቱን በሙሉ እግዚአብሔርን እናከብር ዘንድ በተለያየ ጊዜ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ያደረገውን ታላላቅ ተዓምራት እናስብ ዘንድ እለታቱን በሙሉ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንባቸው ስርዓትን ሰርተውልናል። 

Monday, December 26, 2011

በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ ኢሳ 9፥2

የዛሬው ሰንበት እንደቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ብርሃን ይባላል። ስያሜው የተሰጠው በቅዱስ ያሬድ ሲሆን ወቅቱም የጌታን መወለድ በተስፋ ይጠባበቁ  የነበሩት የአዳምና የልጆቹን ደጅ ጥናትን የምናስታውስበት ነው። በመሆኑም ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሃኒ (  ብርሃንህንና እውነትህን ላክ እነርሱ ይምሩኝ። መዝ 43፥3) ብሎ ተናግሯል። ስለሆነም ቤተክርስቲያናችን የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስቀድማ ለልጆቿ ጾም ጸሎት እያደረጉ ደጅ እንዲጠኑ ታዛለች።

 የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በማፍረሱ ምክንያት ለ5500 ዘመን በዲያቢሎስ ባርነት ተይዞ በጨለማ አገዛዝ ስር ወድቆ ይኖር ነበር። ይሁን እንጅ እግዚአብሔር አምላክ  የሰው ልጅ ደካማ በመሆኑ በዲያቢሎስ ክፉ ምክር ተታሎ እንደወደቀ ያውቅ ነበርና ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ነግሮት ነበር። በመሆኑም እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ አዳምና ከእርሱ በኋላ የነበሩት ልጆቹ በሞተ ስጋ ላይ ሞተ ነፍስ ተጭኗቸው በሲኦል በዲያቢሎስ ተረግጠው  ይኖሩ ነበር።

Saturday, December 17, 2011

ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን

                                      << ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሰላም ጸልዩ >> 

ሁልጊዜ በስርዓተ ቅዳሴያችን ላይ የሚነገር አዋጅ ነው።  በሰው ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነገር ነገር ብዙ ጊዜ ክብርና ቦታ አይሰጠውም ስለዚያም ይመስላል ብዙ ሰው ይህ አዋጅ ሲታወጅ የተለመደ ስለሆነ ብቻ የዲያቆኑ የአገልግሎት ድርሻ መሆኑን ከመገመት ያለፈ ቦታ የማንሰጠው።