Thursday, February 17, 2022

"ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ቃል ኣትናገር!"

በሰው ላይ መፍረድ ኃጢአት መሆኑን አውቃለሁ  እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ካህን ለማናቸውም ኃላፊነት ላይ ላሉ ወገኖች የገቡትን ቃልኪዳን አክብረው ኃላፊነታቸውን በአግባብ ተወጥተው ፍጻሜያቸው እንዲያምር የዘወትር ጸሎቴ ነው።

ነገር ግን ሰዎችን ከስህተት መንገድ እንዲመለሱ መምከር በጎነት ነው በተጨማሪም እንኳን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ
መምራት ይቅርና ቤተሰብን ማስተዳደር ከባድ እንደሆነ እረዳለሁ ነገር ግን ያሉበትን ኃላፊነት በመዘንጋት የግልን ወይም የኔ የሚሉዋቸውን ወገኖች ብቻ ሃሳብ ማንጸባረቅ አርቆ አለማሰብ በመሆኑ ምክረ ሃሳብ መስጠት ያስፈልጋል። በተለይ ብዙ ገንዘብ እየተከፈላችሁ ባለስልጣናትን በማማከር ሙያ ላይ የተሰማራችሁ ወገኖች ለሰዎቹ ብላችሁ ሳይሆን ለህሊናችሁ ስትሉ መልካም ነገር ማማከርን ገንዘብ ብታደርጉ መልካም ነው። መሪዎች ሁልጊዜ መዘንጋት የሌለባቸው ነገር ቢኖር ሲወለዱ በተፈጥሮ ይዘውት የመጡት ከሌላው ህዝብ ምንም የተለየ ነገር የሌለ መሆኑን ነው ክብርና ስልጣኑ እግዚአብሔር ሲፈቅድ እንዲሁም የራስ ጥረት ታክሎበት ህዝብ አምኖና አክብሮ ሲሾመን ከፍታ ላይ እንቀመጣለን ህዝብ በቃ ያለለት ወደ ቀድሞ ማንነት መመለስ አለ። ምናልባትም ኃላፊነትን ባግባቡ ካልተወጡ ከሰውነት በታችም መሆን አለ።



ስለዚህ ህዝብን የሚመራ ሰው የሁሉንም ስሜትና ፍላጎት ማዳመጥ ይገባዋል ከዚያም በአግባብና በስርዓት ሁሉም መብቱ እንዳይነካ ዋስትና የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ማጋነን አይሁንና በህዝባችን መካከል ከትላንት እስከዛሬ ያለው መለያየትና መጠላላት የመጣው በመሪዎች አቋም ማጣት ይመስለኛል ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ለመምራት ወንበር ላይ ተቀምጠው እገሌ ለተባለ መንደር ሲወግኑ ሌላውን ለማኮሰስ ሲጥሩ ይታያሉ ይህ የተቀመጡበትን ኃላፊነት መዘንጋት ነው እንደኔ እግዚአብሔር ከመንደር አውጥቶ የሀገር መሪ ካደረገን ሀገርን መምራት እንጅ ወደ ሰፈር መመለስ ጥሩ አባዜ አይደለም።