Monday, January 22, 2018

በሥጋ እየሞትን በመንፈስ እየኖርን እግዚአብሔርን እናመልካለን።



ትላንት የተከበረው የጥምቀት በዓል በሀገራችን በኢትዮጵያ እና በሌችም ሀገራት የነበረው ገጽታ ደስታም ሀዘንም የቀላቀለ ነበር። የበዓሉን አከባበር በተለያዩ መገናኛዎች ስንመለከት በደስታ አክብረው ወደ ቤታቸው የተመለሱ እንዳሉት ሁሉ ህይዎታቸውን ያጡና በሀዘን በለቅሶ ላይ ያሉ ወገኖቻችን እንዳሉ ለማየት ችለናል። የሚገርመው ከዚህ ቀደም የክርስቲያኖች ደም ሲፈስ የነበረው በአረቡ ሀገራት ነበር። የአሁኑ ግን የተገላቢጦሽ በአረብ ኢምሬትስ በሰላምና በደስታ በድምቀት ሲያከብሩ ባየንበት ዓይናችን የክርስቲያን ደሴት በተባለችው ኢትዮጵያ የወጣቶች ደም ሲፈስ፣ የእናቶች እንባ ሲረጭ፣ የቃልኪዳኑን ታቦት በተሸከሙ ካህናት ላይ የአድማ መበተኛ ጭስ ሲወረወር ለማየት በቃን።

ይህ ነገር በእኔ መረዳት የቤተክርስቲያንን ሥም ለማጉደፍ የተሰራ ተንኮል እንደሆነ ይሰማኛል። በየእለቱ ስለ ዓለም ሰላም የምትጸልይና የምታስተምር ቤተክርስቲያን ሰላም አስከባሪ ምን ያደርግላታል?። ሰበብ ተፈልጎ የንጹሃንን ደም ለማፍሰስ ታስቦ የተደረገ ይመስላል። እኛ ስናውቅ የኢትዮጵያ ፓሊሶች በጥምቀት እለት እንኳን መሳሪያ ተኩሰው ሰው ሊገድሉ ይቅርና በራሳቸው ያለ ኮፍያ አውልቀው ከህዝቡ ጋር የሚዘምሩ ነበሩ። ታቦት የተሸከሙ ካህናት ላይ የሚተኩስ ኢትዮጵያዊ እያፈራን ነው ማለት ነው? እንንኳን ከርስቲያኑ ሙስሊሙ ለእግዚአብሔር ታቦት ክብር ይሰጥ እንደነበር እናውቃለን።