በዓለማችን ብዙ ሰው በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ ይመጣል። የማያውቁት ሃገር አይናፍቅም የሚለው ተረት ለአሜሪካ አይሰራም። ከሚያውቃት ይልቅ የማያውቃት የሚናፍቃት ሃገር አሜሪካ ነች ቢባል አይጋነንም። የሃገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች፣ በልዩ ልዩ መንገድ የሚገቡ ምሁራንና ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስራና በንግድ በህክምና በመሳሰለው ምክንያት ወደዚች ምድር ይመጣሉ። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ለመግባት ስናስብ አስቀድመን ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት እንቸገራለን። እንድንመጣ የሚረዳን ቤተሰብም ብዙ ገንዘብ ከፍሎ ከሃገራችን እንድንወጣ እንጅ የሚጥረው በሃገራችን ያለ አሜሪካ ውስጥ የሌለ ነገር እንዳለ አይነግረንም። ሁልጊዜ እኛ እራሳችንን ድሃ ብለን መቁጠር ይቀናናል። እርግጥ ነው በሃገራችን ብዙ ድሆች ይኖሩ ይሆናል፥ ነገር ግን አሜሪካም ጥቂት ድሆች እንዳሉ ልናውቅ ይገባል። ጠንክሮ ካልሰሩ ባግባቡ ኑሮን መምራት ካልቻሉ አሜሪካ ውስጥ ድሃ ብቻ አይደለም የሚኮነው ወንጀለኛም ነው።