ባለንበት ዘመን የብዙዎቻችን ጥረትና ድካም ሰውን ለማስደሰት መሆኑ እሙን ነው። ሰው ከተደሰተ እግዚአብሔር ይደሰታል ብለንም እናምናለን። እውነት ነው ለሌላው በጎ ማሰብ ከዚህ የሚበልጥ በረከት የለም። ነገር ግን የሰው ፍላጎት የማይገታ ስለሆነ ዛሬ ብናስደስተው ነገ ይከፋብናል። ሰው ሲባል ሁሉንም ያጠቃልላል ለምሳሌ ባል ሚስት ልጅ እናት አባት እህት ወንድም ባልንጀራ ወ ዘተ ነገር ግን እውን ሰውን ደስ ማሰኘት ይቻላል? ሰው ስሜታዊ ነው ስሜት ደግሞ አንድ ጊዜ ይሞቃል አንድ ጊዜ ይቀዘቅዛል። ብዙ ሰዎች ሰውን ለማስደሰት መልካም ሆኖ መገኘት በቂ መስሏቸው ለሰው ሲሉ የህይዎት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ይደርሳሉ ነገር ግን ለሰው ልጅ ዘላቂ ደስታ መስጠት አይችሉም። አንዳንዶች እግዚአብሔርን ፈልገው ሄደው የሰው አገልጋይ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። የነዚህ ሰዎች ችግር እግዚአብሄርን መፈለጋቸው ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈልጎ ለማግኘት የሚያስፈልገው እምነት እና መንፈሳዊ እውቀት ስለሚጎላቸው ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይገናኙ የሚፈልገው ሰይጣን የሰው አገልጋይ ያደርጋቸዋል። ከዚያም ከሰው የሚገጥማቸው ፈተና ደስታቸውን ያርቅባቸዋል። ተስፋ ይቆርጡና እግዚአብሔርን መፈለግ አቁመው አሰናካይ እስከመሆን ይደርሳሉ። ዛሬ ከማን ወገን እንደሆኑ በማይታወቁ የበግ ለምድ ለብሰው በመጡ ባህታውያን ነን፣ መነኮሳት ነን ካህናት ነን በሚሉ አስመሳዮች ደስታቸውን ተነጥቀው በተመሳቀለ መንገድ ላይ የቆሙ ብዙዎች ናቸው። ለሰው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የሚቀይሩ፣ ለሰው ሲሉ ከቤተእግዚአብሔር የሚቀሩ፣ ለሰው ሲሉ ከአላማቸው ወደኋላ የሚሉ ወ ዘ ተ ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው መልካም እንዳደረጉ ያስባሉ ። ነገር ግን ለሰው የምናደርገው መልካም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግኝኙነት መሰናክል እስካልሆነን ጊዜ ድረስ ብቻ ነው።