Wednesday, August 8, 2012

እንደ ሙሴ ያለ መሪ


ወደ ሃሳቤ ከመግባቴ በፊት ጥቂት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ህይዎት ላነሳ እዎዳለሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላቅ ስምና ዝና ካላቸው ሰዎች ከፊት ልናስቀምጠው እንችላለን። ሊቀነቢያት ሙሴ ከመወለዱ አንስቶ እስከ ህልፈተ ህይዎቱ ድረስ እግዚአብሔር ታላላቅ ስራዎችን ከእርሱ ጋር ሆኖ ይሰራ ነበር።

እስራኤል ዘስጋ  በግብጽ ባርነት ሳሉ ይደርስባቸው ከነበረው ሰቆቃ አንዱ ወንድ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የተከለከለ ነበር። ማንኛውም ልጅ ወንድ ሆኖ ከተወለደ ይገደል ነበር። ታዲያ በዚህ ዘመን ነበር ሊቀነቢያት ሙሴ የተወለደው። አስቀድሞ  በእግዚአብሔር የተወሰነ ስለነበር በባህር ቢጣልም እንኳን አንዳች ሳይነካው በህይዎት ከባህር ሊወጣ ችሏል። ከዚህም በላይ በእግዚአብሔር ጥበብ በቤተ መንግስት በእንክብካቤ  የንጉሱ ልጅ እየተባለ ነው ያደገው። ነገር ግን እሱ በቤተመንግስት ተደስቶ ቢኖርም በወገኖቹ ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ እለት እለት ያንገበግበው ስለነበር። የንጉስ ልጅ መባልን አይፈልግም ነበር። በኋላም  ወገኖቹ  በስቃይ ላይ እያሉ እኔ በቤተመንግስት የላመ የጣፈጠ አልበላም አልጠጣም ብሎ ወሰነ።  የህዝቡን ግፍና መከራ ለማየት በሄደ ጊዜ አንድ ግብጻዊ እስራኤላዊውን ሲደበድበው አገኘው ። በልቡ ውስጥ ቁጭት  ስለነበረው ግብጻዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ታድጎታል። ነገር  ግን ይህን በማድረጉ  ከጠላት ያዳነው ሰው መልሶ  አሳልፎ ሊሰጠው እንደሚችል በመረዳቱ ከቤተመንግስት ኮብልሎ  ወደ ምድያም ምድር ተሰደደ ።